“ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት በማረጋገጥ ረገድ የመጨረሻ አማራጮች ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው

11

ፍኖተሰላም: ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር የፍርድ ቤት ነጻነት እና ገለልተኛነት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ባለው ፋይዳ ዙሪያ ለዳኝነት እና ፍትሕ አካላት ሥልጠና እየሰጠ ነው።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚው እና ሕግ አሥፈጻሚው አካል በሕገ መንግሥቱ፣ ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው እና በተቀበለቻቸው ስምምነቶች ዕውቅና ያገኙ የሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና የማሰከበር ኅላፊነት አለበት ብለዋል።

በዚህ ረገድ የፍትሕ አካላት ሚና ግንባር ቀደም መኾኑን ነው የተናገሩት። ፍርድ ቤቶች የሰብዓዊ መብትን ጨምሮ ሕግ የመተርጎም እና ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የማድረግ ኅላፊነት አለባቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት በማረጋገጥ ረገድ የመጨረሻ አማራጮች ናቸው” ነው ያሉት።

የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በተሟላ ሁኔታ ለማስከበር እና ለማክበር ጠንካራ የኾኑ ነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። የዳኝነት ነጻነት እና የዳኞች ከለላ ጠንካራ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶችን በመገንባት ሂደት ሚናው የጎላ እንደሚኾንም ጠቁመዋል።

ነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም እና የዳኝነት ነጻነት እና የዳኞች ከለላ ለዳኞች ጥቅም ተብለው የሚወጡ አይደሉም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ዳኞች በሕግ ላይ በመመስረት እና ለሕሊናቸው ብቻ በመታመን ከፍርሃት እና ካልተገባ ጫና ነጻ ኾነው ፍትሕን እንዲያረጋግጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የዳኝነት ገለልተኛነት እና ነጻነት መከበር የሰብዓዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማክበር እና ለማስከበር ወሳኝ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። የዳኞችን አቅም ለመገንባት የክልሉ መንግሥት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚሰጡት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በተጨማሪ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፈጣን እና ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት እና የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ዲጂታል ማንነት ተስፋ ሰጪ ከሆነው ፈጠራ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሠረታዊ ምሦሶ ተሻሽሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleፋይዳ 9 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር በዲጂታል ግብይት እንዲዘዋወር እያገዘ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገለጹ።