“በሀገራችን ካሉ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብት ስብራቶች ውስጥ አንዱ ብልሹ አሠራር ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

6

ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከጸረ ሙስና ጥምረት አባላት ጋር የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ የሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን ለመከላከል ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ጥምረት መቋቋሙን ገልጸዋል።

ዓላማውም በተቋማት የሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን ለመከላከል መኾኑን አንስተዋል። ባለፉት አራት ወራት በዘርፉ እንደየ ተቋማቱ ባህሪ የተሠሩ ሥራዎችን ለመገምገም እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም ለመነጋገር መኾኑን ጠቁመዋል። የአንዳንድ ተቋማት በጸረ ሙስና ትግል ሥራው ውስንነት እንደታየባቸው እና በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን በማንሳት ለመማማር እንደኾነ ተናግረዋል።

ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመታገል ድክመት በኖረ ቁጥር ሀገር አደጋ ላይ እንደምትወድቅ ያነሱት ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱንም ገልጸዋል። ብልሹ አሠራር እና ሙስናን ለመታገል የተቋማት በቅንጅት መሥራት ለነገ የማይባል ነው ብለዋል። የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ለመጀመር በሂደት ላይ ነው፤ ትምህርት ቤቶች ላይም በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ እና የጥምረቱ ሰብሳቢ ፋንቱ ተስፋዬ “በሀገራችን ካሉ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት ስብራቶች ውስጥ አንዱ የሥነ ምግባር ብልሽት እና ብልሹ አሠራር መኾኑን” ገልጸዋል። የታቀዱ ተግባሮች እንዳይፈጸሙ ዋና ማነቆ የኾነው የሥነ ምግባር ብልሽት በአንድ ጀንበር ባይስተካከልም ሁሉም ተቋማት በመረባረብ የጋራ ልማት እና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

ከሥነ ምግባር ግንባታ እና ጸረ ሙስና ትግል አኳያ የተሠራው ሥራ አነስተኛ ነው ብለዋል። የሥነ ምግባር ብልሽት እና ሙስና የመጨመር አመላካቾች እንዳሉም ጠቅሰዋል። የሕዝብ ጥያቄዎች እና ጩኸቶች በርካታ መኾናቸውንም አንስተዋል። የሕዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩል ገና ይቀረናል ያሉት አፈ ጉባኤዋ የተጠናከረ ሕዝብን የሚያማርር የሥነ ምግባር ብልሽት እና የሙስና ተግባር እንደሚታይ ገልጸዋል። በቀናነት እና በሐቅ የሚያገለግል አካል ቢኖር እንኳ የብልሽቱ ጫና እንደሚያድርበት ነው የተናገሩት።

ሁሉም ተቋማት የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ትግል ሥራዎችን በትኩረት ካልሠሩ አደጋው ለሀገር እየተረፈ መኾኑን አንስተዋል። ይኹንና ችግሩን በአንድ ተቋም ብቻ ሳይኾን ሁሉም እንዲተጋገዝ ጥምረቱን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት። እኛ በሠራን ቁጥር ሕዝቡ በቀናነት ይተባበራል ብለዋል።

የሕዝቡን ፍላጎት፣ ጥቆማ እና ትብብር ተጠቅሞ በመሥራት በኩል ግን ውስንነቶች መኖራቸውን ነው አፈ ጉባኤ ፋንቱ የገለጹት። የጥምረቱ አባላት ሕዝብን በማሳተፍ መሥራት፣ ሌሎቹም ወደ ትግሉ እንዲቀላቀሉ እና መልካም ተሞክሯቸውን ማስፋት እንድኹም በመልካም አሥተዳደር እና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሰላምን ማስፋት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየንግዱ ማኅበረሰብ ምርትን በፍትሐዊነት በማቅረብ ማኅበራዊ ኀላፊነትን እንዲወጣ ተጠየቀ።
Next article“ዲጂታል ማንነት ተስፋ ሰጪ ከሆነው ፈጠራ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሠረታዊ ምሦሶ ተሻሽሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)