
ጎንደር: ግንቦት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አምባ ጊዮርጊስ ከተማ አሥተዳደር 90 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እና ለንግድ ሥራ የሚውሉ ሸዶች ናቸው የተመረቁት።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ መንግሥት በችግሮችም ውስጥ ኾኖ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በአምባ ጊዮርጊስ ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው በጋራ ጥረት መኾኑን ማሳያ ናቸው ብለዋል።
አሁን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም በመስዕዋትነት የመጣ ነው ያሉት ኀላፊው ይህን ዘላቂ ለማድረግ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመኾኑ ነዋሪዎቹ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ
በዞኑ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና በመንግሥት ድጋፍ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በአምባ ጊዮርጊስ ከተማ 90 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው የልማት ሥራዎችን መመረቃቸውንም ገልጸዋል። እንደ ዞን በአንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት በሚል የልማት ሥራዎች እየተተገበሩ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ከሰጠው ዕቅድ በላይ እየተሠራ መኾኑን ነው ያስታወቁት።
ከዚህ በፊት በማኅበረሰቡ ዘንድ ሲጠየቁ የነበሩ የልማት ጥያቄዎች በተሠሩ የልማት ተግባራት ምላሽ ማግኘታቸውን የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ከመንግሥት ጎን ኾነው እገዛ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን