
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የባሕርዳር ከተማ ከንቲባ መቶ አለቃ ዓባይነህ ኢሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት በባሕር ዳር ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ተፈጽሟል።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያመላክተው መቶ አለቃ ዓባይነህ ኢሳ ከአባታቸው ከአቶ ኢሳ ገብረ ሃና እና ከእናታቸው ከወይዘሮ የሻረግ ዓለሙ በአዲስ አበባ ከተማ በ1937 ዓ.ም ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
መቶ አለቃ ዓባይነህ በነበራቸው የሀገር ፍቅር ስሜት የተነሳ በ1959 ዓ.ም በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ተቀጥረው ከወታደርነት እስከ ሕክምና ሥራ አገልግለዋል፡፡ በወታደርነት ሙያ ባሳዩት የላቀ አፈጻጸም የአስር አለቃ ማዕረግ እድገት ማግኘታቸውን የሕይወት ታሪካቸው አትቷል፡፡
በወታደራዊ ግዳጅ አፈጻጸም፣ በፖለቲካ ብስለት እና በተልዕኮ አፈጻጻም ውጤታማነትታቸው ተገምግሞ በንጉሡ አሥተዳደር በ1964 ዓ.ም በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር የባቲ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ኾነው ተሾሙ።
መቶ አለቃ ዓባይነህ የቀዩ ጦር ሠራዊት ሲቋቋም ጦሩን በከፍተኛ ጀብዱ መርተዋል ይባልላቸዋል፡፡ በሁርሶ ወታደራዊ የማሠልጠኛ ተቋም የሚሰጠውን የመኮንንነት ኮርስም በላቀ ውጤት በማጠናቀቃቸው በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ መመረቅ የቻሉ ናቸው፡፡ የቀዩን ጦርም በመምራት በሰሜን ግንባር ተዋግተዋል፣ አዋግተዋልም፡፡
መቶ አለቃ ዓባይነህ በ1970 ዓ.ም የጎጃም ክፍለ ሀገር ፖሊስ መምሪያ የፖለቲካ ኀላፊ ኾነው እንዳገለገሉም ታሪካቸው ያስረዳል። በአሥተዳደራቸው ብቃት እና በሕዝብ በነበራቸው ተቀባይነት የተነሳም ወደ ሲቪል አገልግሎት በመዘዋወር በ1971 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ምክትል አውራጃ አሥተዳደሪ በመኾን ሠርተዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በአዲስ መልክ ሲዋቀርም ከምክትል አሥተዳዳሪነት ወደ ከንቲባነት ዕድገት አግኝተው ከ1973 እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ በከንቲባነት ማገልገል የቻሉ ታላቅ ሠው ነበሩ።
በባሕር ዳር ከተማ ከንቲባነት ዘመናቸውም የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በባሕር ዳር በነበራቸው ጉብኝት የከተማዋ ቁልፍ ችግር የንጹሕ መጠጥ ውኃ መኾኑን አስረድተው ችግሩ እንዲፈታ የተጉ መሪ እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
መቶ አለቃ ዓባይነህ ኢሳ በ1981ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር የጓጉሳ ወንበርማ ሽንዲ ወረዳ አሥተዳደሪ ኾነውም አገልግለዋል፡፡ ከ1996 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የአማራ ክልል ስፖርት ምክር ቤት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና በኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ውስጥ በተለያዩ ኀላፊነቶች ሠርተዋል፡፡
የወጣት እግር ኳስ ፕሮጀክት በክልሉ እንዲስፋፋ፣ ባሕር ዳር ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ፣ አውስኮድ፣ ወልዲያ እና ደሴ ከነማ እንዲፈጠሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገራል።
የክልሉ ክለቦቹ ወደ ፕሪምዬር ሊግ እንዲገቡም ዋጋ የከፈሉ መሪ መኾናቸውም በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ተወስቷል፡፡ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን የመሠረተ ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባር ቀደሙ ሰው ነበሩ።
በ1964 ዓ.ም ዘርፈሽዋል ዘለቀ ጋር በወግ ማዕረግ ትዳር የመሠረቱት መቶ አለቃ ዓባይነህ ለ53 ዓመታት በትዳር በመኖርም የሰባት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
መቶ አለቃ ዓባይነህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክማና ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ግንቦት 9/2017 ዓ.ም አርፈዋል።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በባሕር ዳር ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በከንቲባነት ዘመናቸው ለከተማዋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በቅን ልቦና ያገለገሉ እንደነበሩ ተናግረዋል።
ትምህርት በከተማው እንዲስፋፋ ሁነኛ ድርሻ ነበራቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረት አድርገዋል ብለዋል፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽዎ አበርክተዋል ነው ያሉት፡፡
“መቶ አለቃ ዓባይነህ ራሳቸውን ሳይኾን ሕዝብን ያገለገሉ የሕዝብ ልጅ ነበሩ” ብለዋቸዋል።
መቶ አለቃ ዓባይነህ የቅርብ ጓደኛ እንደነበሩ የነገሩን ሌትናል ኮሎኔል ዓለሙ መብራቱ የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር መቶ አለቃ ዓባይነህ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ በመኾን ጠላትን ተፋልመው የዛሬቱን ኢትዮጵያ ለዚህ ትውልድ አስረክበዋል ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ግርማው መንግሥቱ መቶ አለቃ የባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድን እዚህ ለመድረሱ የእሳቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን