
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብሎም በክልሉ ለተገኘው ሰላም የወጣቱ ሚና የላቀ እንደ ነበር ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል፡፡ አኹን የተገኘውን ሰላም ለማጽናት ከወጣቶች ጋር በቅርበት እንደሚሠራም አረጋግጧል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በክልሉ የዘለቀው የሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ተዛብቶ የኑሮ ውድነት ተባብሷል፡፡ የትምህርት ተቋማት ተዘግተው ታዳጊዎች አልባሌ ቦታ እንዲውሉ ኾነዋል፡፡
የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ ኾነው ሕሙማን በበረታ ስቃይ ውስጥ እንዲያልፉ ተገድደዋል፡፡ የክልሉ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር ኾኗል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ቅንጦት እንዲኾንባቸው ተደርጓል፡፡
የግብርና ግብዓት በወታደር ታጅቦ አርሶ አደሩ ቀየ ድረስ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ነባር ማኅበራዊ እሴቶች ተሸርሽረው ገስጾ ማሸነፍ፤ መክሮ መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይም ተደርሶ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ የወንድማማቾች ግድያ ክልሉን በርካታ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡
በጥቅሉ ባለፉት 22 ወራት ክልሉ የመጣበት እና ያለፈበት ውጣ ውረድ ቢሰላ ትርፉ ኪሳራ ብቻ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜያት በየደረጃው የተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች የችግሩን ጥልቀት እና ክልሉን ወደ ኋላ የጎተተበትን እርቀት በሚገባ ማሳየታቸውን ተከትሎ አንጻራዊ ሰላም በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ሰፍኗል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ታጥቀው ጫካ የገቡ ወገኖች የሰላም አማራጮችን ተቀብለው ወደ መንግሥት እየገቡ ነው፡፡ በእርግጥም እስከ ቀበሌ እና ጎጥ ድረስ የወረደው ሕዝባዊ ውይይት እና ምክክር በክልሉ ሰማይ ስር የሰላም አየር እንዲነፍስ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ከሰሞኑ ከ90 በላይ የሕዝባዊ መድረክ ውይይቶችን እና የሰላም ምክክሮችን በስድስቱም ክፍለ ከተሞች ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ሲያካሂድ የቆየው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የወጣቶች እና ሴቶችን የማጠቃለያ መድረክ ዛሬ አካሂዷል፡፡
ቁጥራቸው የበዛ ወጣቶች እና ሴቶችም በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ለከተማቸው ሰላም ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
“በጦርነቱ ለነገ ልንማርባቸው እንጂ ነገ እንድናስታውሳቸው የማንፈልጋቸው ጉዳቶችን አሳልፈናል” ያለችን እና ከፋሲሎ ክፍለ ከተማ የመጣችው ወጣት ክቤ የኋላ አኹን ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል ብላለች፡፡
የከተማዋ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ተከትሎ በርካታ ወገኖች ሕይዎትን መግፋት አዳጋች ኾኖባቸው ነበር ያለችው ወጣት ክቤ አኺን ላይ የሚስተዋለው የሰላም አየር ተስፋ ሰጭ ኾኗል ብላለች፡፡
የተገኘውን ሰላም በማጽናት ባሕር ዳር ከተማን ወደ ቀደመ ውበቷ እና ሰላሟ ለመመለስ ውይይት እና ምክክር ያስፈልጋል ነው ያለችው፡፡ የክልሉ ሕዝብ እንዲመለሱለት የሚፈልጋቸው ጥያቄዎች አሉት ያለችው ወጣቷ ጥያቄዎቹን ለማስመለስ በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግም አንስታለች፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ከሚደረገው ትግል በተጨማሪ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የገለጸው ደግሞ ከጣና ክፍለ ከተማ የመጣው ወጣት ነጻነት ገበየሁ ነው፡፡
የሰላም እጦቱ ከጎዳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው ያለው ወጣት ነጻነት በከተማ አሥተዳደሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ብሏል፡፡ አኹን ላይ በከተማ አሥተዳደሩ እየተወሰዱ ያሉ ጅምር ሥራዎችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ጌታቸው ግዛቸው በክልሉ ለተገኘው ሰላም የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡ አኹን ያለውን ሰላም ለማጽናትም ከወጣቶች ጋር በቅርበት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከወጣቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፤ በውይይቱም ከተማ አሥተዳደሩ ከወጣቶች ጋር በቅርበት እንደሚሠራ አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ በተደረገው የወጣቶች እና ሴቶች ማጠቃለያ መድረክ ላይም ቁጥሩ የበዛ የከተማዋ ወጣት ተሳታፊ ነበር ያሉት አቶ ጌታቸው የወጣቱን ጉልበት እና የሴቶችን ብልሃት ለሰላም ማስፈን ሥራው ጉልበት አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በወጣቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን