
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ ለዞኑ ጤና መምሪያ ደግሞ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶክተር) ለአብመድ እንደገለጹት 500 ሊትር ዘይት፣ 37 ኩንታል የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች እንዲሁም 200 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ድጋፉም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ለደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያም የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። የሕክምና ባለሙያዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲያስችሉ ታስቦ የተደረጉት የቁሳቁስ ድጋፍ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ወጭ እንደተደረገባቸው ዶክተር አነጋግረኝ ገልጸዋል፡፡
የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አበበ እምቢያለ ዩኒቨርሲቲው ለከተማው ማኅበረሰብ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመሥግነዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በወረርሽኙ ምክንያት በባሰ ችግር ውስጥ የሚገኙ 1 ሺህ 310 ሰዎች በመለየት እንደ ችግር መጠናቸው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ከንቲባው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲም ለ200 ሰዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ለመተማ ለይቶ ማቆያም ዛሬ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እስካሁን ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ድጋፍ ማድረጉን ዶክተር አነጋግረኝ አስታውቀዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከመሥራት ባለፈ ለደቡብ ጎንደር ዞን “የኳራንታይን ማዕከል” በመሆን እያገለገለ መሆኑም ይታወቃል፡፡
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከደብረ ታቦር