ሕዝቡ ሰላሙን እየጠበቀ በልማቶች ተሳታፊ እንዲኾን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት የከተማዋን የልማት ሥራዎች ተዘዋውረው እየተመለከቱ ነው።

የምክር ቤት አባላት ከተማዋን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመጠበቅ የተሠራውን የካሜራ መከታተያ፣ በዲፖ አካባቢ የተሠራውን የጣና መናፈሻ፣ ከተማ አሥተዳደሩ ያስገነባውን የሕዝብ ቅሬታ መቀበያ የስልክ ጥሪ ማዕከል፣ ከመብራት ኀይል እስከ አየር ማረፊያ እየተሠራ ያለውን ዘመናዊ አሥፋልት መንገድ፣ ውብ ኾኖ ተገንብቶ አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘውን የዓባይ ድልድይ፣ ከአልማ እስከ ወተር ፍሮንት ሆቴል የሚሠራው አዲስ መንገድ፣ እና የጣና ዳርቻ አረንጓዴ ልማቶችን ነው እየጎበኙ የሚገኙት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት የምክር ቤቱ አባላት በትላንትናው ዕለት የዘጠኝ ወር ሥራ አፈጻጸምን ከገመገሙ በኃላ ዛሬ ደግሞ በተግባር እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶችን እየተመለከቱ ነው።

በከተማዋ ውስጥ በርካታ የሕዝብ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው፤ ለአብነትም 22 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ እየተገነባ ነው ብለዋል። የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችም ተማሪዎች እና ወጣቶች የሚያነብቡባቸው፣ እንግዶች አረፍ ብለው ከተማዋን የሚያዩባቸው፣ የሀገር ሽማግሌዎችም ጥላ ላይ አርፈው የተጋጩትን በቆየው ብሂል የሚያስታርቁባቸው ናቸው ብለዋል።

የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች የከተማዋን ውበት ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለቱሪዝም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው፣ ለነዋሪዎችም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያስገኙ ናቸው ነው ያሉት።

መንግሥት የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶችን እየገነባ መኾኑን ጠቁመው ሕዝቡም ሰላሙን እየጠበቀ በልማቶች ሁሉ ተሳታፊ እንዲኾንም ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምክር ቤት አባላት በከተማዋ የሚከናወኑ ልማቶች ለታለመላቸው አገልግሎት እንዲውሉ ሕዝቡ መንከባከብ ይገባዋል ብለዋል። ልማቶቹ ውበታቸው ተጠብቆ ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የምክር ቤት አባላቱ አሳስበዋል።

ባሕር ዳር ገና ብዙ መልማት አለባት፤ ሕዝቡ ሰላሙን አስጠብቆ በሚችለው መንገድ ሁሉ በልማቱ ተሳታፊ መኾን እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የወጣቶች እና ሴቶች ሚና አይተኬ ነው።
Next article“የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)