
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከስድስቱም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ወጣቶች እና ሴቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
ባለፋት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል። ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ውይይቶች በየደረጃው እየተካሄዱ ነው።
“የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ጌታቸው ግዛቸው ክልሉ ባለፋት ዓመታት በበርካታ ምስቅልቅል ችግሮች ውስጥ ማለፉን አንስተዋል።
“በሰሜኑ ጦርነት ክልሉ የከፈለውን ዋጋ ታውቃላችሁ” ያሉት አቶ ጌታቸው ያ ጦርነት ካስከተለው ዳፋ በአግባቡ ሳናገግም ወደ ግጭት መግባታችን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች አጋልጦናል ነው ያሉት።
በሰላም እጦቱ ባሕር ዳር ከተማ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ዋጋ መክፈሏንም አንስተዋል። አሁን ላይ የተገኘውን ከአንጻራዊ የተሻገረ ሰላም ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የተገኘውን ሰላም ለማረጋገጥ ደግሞ ወጣቶች እና ሴቶች ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በግጭት ውስጥም ተሁኖ የከተማዋን እድገት እና ምቾት ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል። በሙሉ ሰላም ውስጥ ብንኾን ደግሞ ምን ልንሠራ እንደምንችል ማሰብ ያስቆጫል ነገር ግን አሁንም በአንድነት ከቆምን ለውጥ ይመጣል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን