
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 29ኛ መደበኛ ጉባኤን እያካሄደ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ሥራዎች ለምክር ቤቱ አባላት ቀርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋን ለነዋሪዎች እና ለጎብኝዎች ምቹ፣ ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ተመራጭ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በትኩረት ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ተቀዳዊው ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል።የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ ባለፈ የከተማዋን መሠረተ ልማት ማፋጠን ላይም ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
የትምህርት ሥልጠና ማስፋፋት እና ማጠናከር፣ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት እና ጥገና፣ የሕገ ወጥ ግንባታ እና የጎዳና ላይ ንግድ የመከላከል ሥራ ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች መኾናቸውን አንስተዋል።
በከተማዋ የኢንቨስትመንት ምህዳርን ለማስፋት እና የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍም ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡን እያማረሩ የሚገኙ የመልካ አሥተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ብልሹ አሠራሮችን ለመፍታት ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
የከተማዋን ደኅንነት ለማስጠበቅ በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች የደኅንነት ካሜራዎች መትከል ተችሏል ብለዋል፡፡
ተቋማት የአካባቢውን ጸጋ ተጠቅመው ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ተኩረት ተደርጎ መሠራቱንም አስገንዝበዋል።
በማኅበራዊ እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይም ከማኅበረሰቡ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መካሄዱን ነው የተናገሩት።
ዓመታት ያስቆጠሩ የሕዝብ ቅሬታዎችንም በጥናት በመለየት እንዲፈቱ መደረጉንም ገልጸዋል።
በቀጣይ በኑሮ ውድነት፣ በሥራ አጥነት፣ በመኖሪያ ቤት፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዩች፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ብልሹ አሠራር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የስማርት ሲቲ ጽሕፈት ቤት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ልማት እና በመልካም አሥተዳደር ዘርፍ በከተማዋ የተከናወኑ ሥራዎች በዝርዝር ለምክር ቤቱ አባላት ቀርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን