
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ሥር የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ሥራ አውደ ራዕይ ዛሬ አካሄደዋል።
የጊዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቴዎድሮስ ብርሃኑ በአውደ ርዕዩ ባለ ቢጫ ቀለም አውሮፕላን እና ሰው አልባ በራሪ አውሮፕላኖችን ሠርቶ ለዕይታ አብቅቷል።
አውሮፕላኑ አካባቢን በልዩ ኹኔታ በመቃኘት እንደ ግሪሳ ወፍ እና የአንበጣ መንጋ ሲከሰት ለይቶ መረጃ ያደርሳል ነው ያለው የፈጠራ ባለቤቱ ተማሪ ቴዎድሮስ።
ይህ አውሮፕላን ከቅኝት ተግባር ባሻገር ጸረ ተባይ መድኃኒት በመርጨትም ለግብርናው ዘርፍ አጋዥ ለመኾን ያስችላል ብሏል።
ሰው አልባ በራሪ አውሮፕላኑም የአየር ላይ ምሥሎችን በማንሳት ለተለያዩ ተግባሮች እንዲውል ተደርጎ መሠራቱን ነው ተማሪው ያብራራው።
የዲያስፖራ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ አሸናፊ ገረመው በበኩሉ በቤት እና ቢሮ ውስጥ የሚገኝን ቆሻሻ ከሰው ንኪኪ ነጻ በኾነ መልኩ የሚያጸዳ የፈጠራ ሥራ ማቅረቡን ገልጿል።
መሳሪያው በሚያጸዳበት ወቅት አቧራ በማያስነሳ እና የአካባቢ አየር በማይበክል ኹኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ መሠራቱን ተማሪ አሸናፊ ተናግሯል።
የኤስ ኦ ኤስ ሴት ተማሪዎች ደግሞ በመማሪያ እና አጋዥ መጻሕፍት እጥረት ለሚቸገሩ ተማሪዎች መጻሕፍትን በተንቀሳቃሽ ሰልካቸው እና በኮምፒዩተር ላይ በቀላሉ የሚያገኙበትን የፈጠራ ሥራ ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በጊዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ክበብ ተጠሪ መምህር ዋለ ዳኘው ፍላጎቱ እና ችሎታው ያላቸውን ልጆች በመለየት በፈጠራ ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች ለፈጠራ ሥራዎች የተመቹ ናቸው ያሉት መምህር ዋለ በእነርሱ ትምህርት ቤት የስካይ ማስተር አውሮፕላኖች እና ሰው አልባ በራሪዎች በተማሪዎች ተሠርተዋል።
ተማሪዎች ከውጭ ሀገር ተሠርተው በሚመጡ መሳሪያዎች በመቆጨት በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት። በዚህም ተስፋ ማሳደራቸውን ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) እንዳሉት ተማሪዎች 84 የፈጠራ ሥራዎችን በአውደ ርዕይዩ አቅርበዋል። ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲያዩት መደረጉ ለፈጠራ እንዲነሳሱ ማስቻሉን ነው የጠቆሙት።
ነገ ደግሞ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀታቸው የተሻሉ ተማሪዎችን ለማፍራት አውደ ርዕዩ ከፍተኛ እገዛ አለው ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቶች ለፈጠራ ሥራ የተመቹ እንዲኾኑ በዕቅድ መመራታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ እንዳስቻላቸው ዶክተር ሙሉዓለም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ እያንዳንዱ የተማረ ዜጋ ልዩ ችሎታውን ተጠቅሞ ራሱን ጠቅሞ ሀገርን እንዲያሻግር ከትምህርት ቤቶች የተጠናከረ ሥራ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሀገር ማደግ የምትችለው በተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎች ነው ያሉት አቶ መኳንንት በቀጣይም ቴክኖሎጂዎች የሚያድጉት በተማሪዎች ሥራ ነው ብለዋል።
እየታየ ያለው የፈጠራ ሥራም ከወዲሁ የሚያበረታታ እንደኾነ ነው የጠቆሙት።
መሰል ሥራዎች በክልል ደረጃም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን