በክልሉ የሚሰራጩ አምቡላንሶች ለጤና አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳሰቡ።

289

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የአምቡላንስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የክልሉ መንግሥት ሦስት አምቡላንሶችን ነው ድጋፍ ያደረገው፡፡ አምቡላንሶቹ የልዩ ኃይል አባላት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እያደረጉት ላለው ጥረት አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸው ተገልጧል፡፡ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ አምቡላንሶቹ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እና ለአጠቃላይ የጤና አገልግሎቶች እንደሚውሉ ተናግረዋል። ከሠራዊቱ ባሻገር ለኀብረተሰቡም አገልግሎት እንዲሰጡ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳደሩ አመላክተዋል።

የጤና አምቡላንሶችን ለሌሎች አገልግሎቶች የሚጠቀሙ ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳደሩ ሠራዊቱ አምቡላንሶችን ለሌሎች አገልግሎቶች ባለማዋል አርአያ እንዲሆንም ጠይቀዋል። የክልሉ ፖሊስና ልዩ ኃይል የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ እያደረጉት ላለውም ጥረትም አመሥግነዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ መልካሙ አብቴ (ዶክተር) ክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት በዚህ ዓመት 235 አምቡላንሶችን ለጤና ተቋማት በመስጠት ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን አስታውሰዋል።

አሁንም በክልሉ የአምቡላንስ እጥረት በመኖሩ በአገልግሎት ላይ ያሉት አምቡላንሶችን ለታለመላቸው አገልግሎት በማዋል ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አምቡላንሶቹ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የኮሮናቫይረስ ታካሚዎችን ፈልጎ በማምጣትና በመጠበቅ ባላቸው ሚና ተጋላጭ እንዳይሆኑና ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮሎኔል ጌታቸው ብርሌ ሠራዊቱ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በድንበሮች እና በለይቶ ማቆያዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አምቡላንሶችን ከሠራዊቱ ባሻገር ለሌሎች የማኀበረሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየኮሮናቫይረስ መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ኃይሉ አስገዳጅ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ፡፡
Next articleደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የምግብ እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።