
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ለሀገራዊ ለውጥ የጤና ባለሙያዎች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት በከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ሥር ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እና ሠራተኞች ጋር የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የጤና ባለሙያዎች በሥራችን ልክ ተገቢ ጥቅማ ጥቅም እና ክፍያ እየተፈጸመልን ባለመኾኑ መልስ እንሻለን ብለዋል። ከሥራው ባሕሪ አንጻርም ባለሙያው ሊያገኛቸው የሚገቡ ነገሮች ምላሽ ያስፈልጋቸዋል የሚሉ ጥያቄዎችም በመድረኩ ተንጸባርቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አብርሃም ዓለሙ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት አሥተባባሪ ናቸው። የሚነሱ ጥያቄዎች መሠረታዊ በመኾናቸው ፈጣን ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። በጤና ባለሙያዎች በኩልም እየገጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች በሰከነ መንገድ ማቅረብ እና ችግሮችን የጋራ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል። ጥያቄዎችም ክቡር የኾነውን የጤና ሙያ ባከበረ እና አገልግሎቶች ሳይቋረጡ መኾን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ የሽንብጥ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ማስተዋል ወልደማርያም የጤና ባለሙያዎች አሁን ካለው የኑሮ ውድነት እና ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ለመኖር ተቸግረን እንገኛለን ብለዋል። እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችም እውነታ ያላቸው እና መሠረታዊ ናቸው ነው ያሉት። ሕክምና የአዕምሮ ሥራ በመኾኑ ባለሙያውን የሚያስቆዝሙ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው ብለዋል። ጥያቄዎች ሲጠየቁ ግን የማኅበረሰቡን አገልግሎት በማያስተጓጉል መንገድ መኾን አለበት ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ዓለም አሰፋ የተጠየቀው የደመወዝ እና የጥቅማጥቅም ጥያቄ የባለሙያው ብቻ ሳይኾን የመሪዎችም ነው ብለዋል። ነገር ግን ጥያቄዎች አግባብ ባለው መንገድ መኾን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት በሚሹ አካላት አጀንዳ ላለመጠለፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል ነው ያሉት።
የሥራ ማቆም አድማ ለአፍታም ከማይፈቀድባቸው ተቋማት ውስጥ ዋናው የጤና ተቋም እንደኾነም ተናግረዋል። ምክንያቱም የጤና ተቋማት የሕይዎት ዋስትና በመኾናቸው እንደኾነ አስረድተዋል። የጤና ባለሙያዎች በችግር ውስጥም ኾነው የሰው ሕይዎትን እያተረፉ እና ዋጋ እየከፈሉ ቆይተዋል በዚህ ልትኮሩ ይገባል ያሉት ኀላፊዋ ይህንን ስም እና ዝና መጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ሀገር በብዙ ዘርፎች ትገነባለች ብለዋል። ሀገርን ሀገር የሚያሰኘው ደግሞ የሰው ልጅ እንደኾነ ገልጸዋል። የሰው ልጅ ክቡር ፍጡር ኾኖ ሳለ የሚፈታተነው የጤና እክል እንደኾነም አስገንዝበዋል። መፍትሔው ደግሞ የጤና ባለሙያዎች መልካም ሙያ እንደኾነም ጠቁመዋል።
“ትውልድን በመገንባት ረገድ የጤና ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደኾነም” ተናግረዋል። ስለኾነም የጤና ሙያ የተከበረ ሙያ እንደመኾኑ መጠን ክብሩን ልንጠብቀው ያስፈልጋል ነው ያሉት። ይህ የሚኾነው ለማኅበረሰቡ በቀናነት የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በተግባር መተርጎም ሲቻል እንደኾነም ገልጸዋል።
ችግሮች አይኖሩም አይባልም ያሉት ምክትል ከንቲባው ሀገር የሚገነባው በችግር ውስጥ አልፎ ነውና እየተቸገራችሁም ቢኾን ሀገር የማሻገር ኀላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ብለዋል። በቀናነት ማኅበረሰቡን ማገልገል ትልቅ ኀላፊነት ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
አሁን ላይ የጤና ባለሙያው ኑሮው እየከበደው እንደኾነ ቢታመንም ሀገርን ማሻገር ላይ ድርሻን መወጣት ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል። ጥያቄዎችም መልክ ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተዋል። የጤናው ዘርፍ ወደ ዲጂታላይዜሽን እየገባ በመኾኑ ዘመኑ የወለደውን የቴክኖሎጅ ውጤት በመጠቀም ማኅበረሰቡን ማገልገል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን