
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊ የከተማዋ ሰላም እና ልማት ዙሪያ እየተወያዩ ነው። ውይይቱ “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ ያለው።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ የአማራ ክልል ሕዝብ በውል የታወቁ ፍትሐዊ ጥያቄዎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ ኀላፊው እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ግን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ እና ሕዝብን ለሌላ ችግር መዳረግ ግን ተገቢ እንዳልኾነም አስገንዝበዋል።
“በነፍጥ የሚፈታ ችግር እና የሚገነባ ሀገር አይኖርም” ያሉት ኀላፊው ይልቁንም ችግሮችን ወደ ጠረጼዛ አምጥቶ ሰክኖ መወያየት እና መፍታት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። መንግሥት ለሰላም ያለውን አቋም በተደጋጋሚ እያሳወቀ ነው፤ ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎችንም በሰላም እየተቀበለ ወደ ልማት እያስገባ ነው ብለዋል። ይህንን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ሕዝብን በሚበድሉት ላይ ደግሞ አሥፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ በማጠናከር የማረም ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ነው፤ ሰላሙን በጋራ እያስጠበቀ ለከተማው ልማትም እየሠራ ነው ብለዋል አቶ ጊዜው። የሚከናወኑ የመንገድ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች የከተማዋ ሰላም መኾን ውጤቶች ስለመኾናቸውም ጠቁመዋል። የባሕር ዳር ሕዝብ ለዓመታት ሲጠይቃቸው የነበሩ የከተማ ልማት ሥራዎች መልስ እያገኙ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የጣና ሐይቅን ውበት በመግለጥ የሕዝብ ማዘውተሪያ ቦታዎች ልማት መከናወኑንም እንደአብነት አንስተዋል።
ሰላምን የሚያውኩ ታጣቂዎች ከየትም አልመጡም፤ ከሕዝብ የወጡ ናቸው ያሉት አቶ ጊዜው ሕዝቡ በመምከር ወደ ሰላም ሊመልሳቸው እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ነዋሪዎች ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በግጭት ምክንያት ብዙ ዋጋ መከፈሉን አንስተው በጋራ በመቆም ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ ነው የተናገሩት። በመሳሪያ የሚፈታ ችግር የለም፤ ይልቁንም የሕዝብን ችግር የሚያባብስ ነው፤ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ጥያቄዎችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መኾን አለባቸው ሲሉም ተወያዮች አንስተዋል።
ግጭቱ በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት መገደቡንም ተናግረዋል። ተዘዋውሮ ቤተሰብ መጠየቅ እና ሠርቶ መለወጥ አዳጋች እንደኾነባቸውም በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
መንግሥት ከመቸውም ጊዜ በላይ ለሰላም ቁርጠኛ ይሁን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም ይምከሩ፣ ይጸልዩ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን በመምከር ወደልማት እንዲመለሱ ያድርጉ ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች። ዳግም በግጭት የሚወድም ንብረት እና የሚጠፋ ውድ የሰው ሕይወት መኖር የለበትም ሲሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!