ሴት መሪዎች ለትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

19

ባሕርዳር: ግንቦት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ”በትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ዙሪያ የሴቶች ሚና” በሚል መልዕክት ከክልሉ ሴት መሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ማሩ ቸኮል ኮሚሽኑ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና አደረጃጀቶች ጋር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በሕጻናት ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ሴቶች በሥነ ምግባራቸው አርዓያ፤ በሙስናም ብዙም የማይታሙ በመኾናቸው ስብዕናቸውን ለመጠቀም ውይይት በማስፈለጉ መድረኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል። ሴቶች ያላቸውን ግላዊ መልካም ባሕሪ ቤተሰባዊ፣ አካባቢያዊ እና ተቋማዊ ማድረግ እንዲችሉ ውይይት ማስፈለጉን ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶች በትውልድ የሥነ ምግባር ቀረጻ ላይ በአዎንታዊ የሚገለጽ ስብዕና እንዳላቸው ገልጸዋል። ሴቶች በሥነ ምግባር ብልሽትም ኾነ በሙስና የሚታሙ አለመኾናቸውን አንስተዋል። ይህን መልካም ስብዕና ወደ ቤተሰብ እና የሥራ ባልደረባ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል። ከሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ትግሉ አኳያም ሴቶች መልካም ስብዕናቸውን ተጠቅመው እንዲሠሩም አመላክተዋል።

ልጆቻችን፣ ወንድሞቻችን እና የትዳር አጋሮቻችን በብልሹ አሠራር ውስጥ ከገቡ ጉዳቱ ተመልሶ እኛው ላይ ነው ያሉት ኀላፊዋ በውይይት የቤተሰብ ሥነ ምግባር ግንባታ ላይም መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ክልሉ በተደራራቢ ችግር ውስጥ ነው፤ ለዚህም በሥራችን እና በተቋማችን በመልካም ሥነ ምግባር አገልግሎት በመስጠት ለችግሮች መፍትሔ የማፈላለግ ኀላፊነት አለብን ነው ያሉት።

በብልሹ የአገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ተጎጂዎች ሴቶች እና እናቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል። ሕዝብን ወክለን ኀላፊነት ላይ የተቀመጥን ሴቶች ብልሹ አሠራርን መታገል እና ማስተካከል አለብንም ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት መኖሩን ያነሱት ኀላፊዋ ሕዝቡ ለከፈለው ግብር በፍትሐዊነት መገልገል አለበት ብለዋል። ለዚህም በደንብ መመከር እንደሚገባ አንስተዋል። አገልግሎት በነጻነት፣ በፍትሐዊነት እና ያለጉቦ እንዲገኝ መምከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ሴቶች ታምነን መሥራት፣ ማገልገል እና መታገል አለብን ነው ያሉት።

ሴቶች የራሳቸው ንጹህነት ብቻ ሳይኾን በተቋማቸው እና በአካባቢያቸው ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በንቃት መታገል እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ለዚህም ውይይት እና ተመሳሳይ መነሳሳት ለመፍጠር መድረኩ መዘጋጀቱን አመስግነዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበከለላ ወረዳ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የከተማዋ ሰላም መኾን ውጤቶች እንደኾኑ ተገለጸ።