የኮሮናቫይረስ መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ኃይሉ አስገዳጅ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ፡፡

152

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከሱዳን ወደ አገር ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ሰው እያስገቡ ለወገን በሽታና ሞት እያከፋፈሉ ያሉ “ኮንትሮባንዲስቶችን” ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሮናቫይረስ መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ኃይል አስጠነቀቀ፡፡

የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ቢሠሩም በአብዛኛው ኅብረተሰብ እየተተገበሩ ባለመሆኑ የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሮናቫይረስ መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ግብረ ኃይሉ የተሠሩ ተግባራትንም ገምግሞ በቀጣይ ተግባራት ላይ ተወያቷል። የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስፈፀም እና ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ሕዝቡ ራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሲያስገነዝብ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጅ በተፈጠረዉ ግንዛቤ ልክ እና ሰው ባወቀው መጠን በመፈፀም በኩል ዝቅተኛ መሆኑን መገምገሙን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

በግምገማው መሠረትም በቀጣይ ሊፈፀሙ የሚገባቸው አስገዳጅ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

1. ከወረርሽኙ መዳን የሚቻለው ግንዛቤው ሲኖር በመሆኑ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለሁሉም የዞኑ ቀበሌዎች ተደራሽ እንደሚደረጉ፣

2. በማንኛውም መሥሪያ ቤት ከዞን እስከ ቀበሌ አገልግሎት የሚሰጥ ሠራተኛ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እና ሳኒታይዘር መጠቀም እንዳለበት፣ አሠሪ መሥሪያ ቤቶች ቁሳቁሱን የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸውና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይጠቀም አገልግሎት መስጠት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

3. ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ድርጅቶች ከድርጅታቸው በር ላይ ደንበኛው ርቀቱን እንዲጠብቅ ገመድ ከመዘርጋት ባሻገር አገልግሎት ሰጭዉ ባለንግድ ድርጅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እና ጓንት የመጠቀም ግዴታ እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

4. በብዛት ተሰባስቦ መሄድም ሆነ መቆም ፈፅሞ እንደማይቻል፣ ይህ ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠርባቸው የሚችሉ ቦታዎች በተለይም የቀን ሠራተኛ ሥራ ፍለጋ የሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ መሰባሰብ የተከለከለ መሆኑንና ከፍተኛ ቁጥጥርም እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡

5. አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ላይ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች መዋያ እና ማደሪያቸው በሚሠሩበት አካባቢ (ለይቶ ማቆያ) ይሆናል።

6. ከኮሮና ቫይረስ መከላከል ተግባር ውጭ የሆኑ መደበኛ የጤና አገልግሎት ተግባራት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አንዳለባቸው፣ በተለይም እናቶችና ሕጻናት ላይ የሚሠራውን ሥራ የበለጠ ማጠናከር እንደሚጠበቅ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

7. ዞኑ ከጎረቤት ሀገር ጋር በየብስ ትራንስፖርት ስለሚገናኝ ከሱዳን ወደ አገር ውስጥ ሰው እያስገቡ ለወገን በሽታና ሞት በዕለት ጥቅም እያከፋፈሉ ያሉ “ኮንትሮባንዲስቶችን” ኅብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን እንዲታገላቸው የጠየቀው ግብረ ኃይሉ በድንበር አካባቢ በሕገወጥ ንግድ የተሰማሩ አካላት ከዚህ አስከፊና ኃላፊነት የጎደለው ድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስቧል፡፡

8. ኮማንድ ፖስቱም ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆንና ኃይሉን በማጠናከር ከጎረቤት ሀገራት ሊገባ የሚችለውን ሰው በመያዝ “ኳራንታይን” እንዲገባ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ አካባቢው ለወባ እና ሌሎች ወረርሽኞች ተጋላጭ በመሆኑ የቅድመ መከላከል ተግባሩን መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር እና መንግሥት የሚያወጣውን መመሪያ በመፈፀም እንዲተባበር ጠይቋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleኢትዮጵያ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡
Next articleበክልሉ የሚሰራጩ አምቡላንሶች ለጤና አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳሰቡ።