በከለላ ወረዳ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።

31

ደሴ: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ወረዳ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። በመንግሥት በጀት፣ በሕዝብ ተሳትፎ እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች የተገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ የውኃ ተቋማት፣ የአርሶ አደሮች ማሠልጠኛ ማዕከል፣ የመስኖ ቦይ እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ መሠረተ ልማቶች ናቸው ተጠናቅቀው ለምረቃ የበቁት።

ከተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ሰንቦ፣ ሻፊ እና ደገር በሚባሉ አካባቢዎች በ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል። በወረዳው ከ20 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በቲርቲራ ከተማ መገንባቱን እና ለግንባታውም የኅብረተሰብ ተሳትፎን ጨምሮ 22 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበት የከለላ ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌታቸው ደምሴ ተናግረዋል።

የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ሥራ መጀመሩ ለረጂም ጊዜ ሲገጥማቸው የነበረውን የውኃ እጥረት እንደቀረፈላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የቲርቲራ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከ13 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ዘመናዊ የአርሶ አደርሮች ማሠልጠኛ ተቋም ተገንብቶ መጠናቀቁን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። የማዕከሉ ሥራ መጀመር የአርሶ አደሩሮችን ክህሎት ለማሳደግ እና ግብርናን ለማዘመን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።

45 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው የመስኖ ቦይ ግንባታ በ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መኾኑም ዋና አሥተዳዳሪው አመላክተዋል። በክልሉ እና በወረዳው መንግሥት በጀት እንዲሁም በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በልጓማ ከተማ መሠራቱን አንስተዋል። ለግንባታውም ከስምንት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

የውስጥ ለውስጥ መንገዶቹ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ በተለይ በክረምት ወቅት ይገጥማቸው የነበረን እንግልት እንደሚያስቀርላቸው የልጓማ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል። የውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለመኖሩ ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ መቆየታቸውን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ የመንገዶቹ መገንባት ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አንስተዋል። አረጋዊያን እና ህጻናት በየዕለቱ ሲገጥማቸው የነበረን ችግር እንደሚያቃልልም ጠቁመዋል።

የውስጥ ለውስጥ መንገዶቹ ግንባታ እንዲፋጠን የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር የልጓማ ከተማ ከተማ እና መሠረተ ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አሕመድ ሙህዬ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ በጉልበት ከማገዝ እና አጥርን አፍርሶ ለሥራው ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ የገንዘብ መዋጮ ማድረጋቸውንም አቶ አሕመድ ገልጸዋል።

በልማት ፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን አማራ ክልል ምንም እንኳን የጸጥታ ችግር የገጠመው ቢኾንም ሰላምን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ ሥራዎች ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

የተመረቁ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የየአካባቢውን ነዋሪዎች የረጂም ጊዜ ጥያቄዎች የመለሱ መኾናቸውንም አስረድተዋል። በቀጣይ የልጓማ እና አካባቢውን ሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የዞኑ አሥተዳደር በትኩረት እንደሚሠራም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

ሕዝቡ የልማት ጥያቄዎቹ በአግባቡ እንዲመለሱለት ሰላሙን መጠበቅና ዘላቂነቱንም ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበትም መልእክት አስተላልፈዋል። የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ለረጂም ጊዜ እንዲያገለግሉ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት መጠበቅ እና መንከባከብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

በወረዳው ተጠናቅቀው ከተመረቁ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሚገለገሉበት የቢሮ ሕንጻ 500 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጪ ለመገንባት በክልል እና በዞን ከፍተኛ አመራሮች የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ፣ የአማራ ክልል ወጣት እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ፣ ሌሎችም የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የየአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- አሊ ይመር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleነጋዴዎች እና ባለሃብቶ መፈናቀላቸው ሊቆም እንደሚገባ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት አሳሰቡ።
Next articleሴት መሪዎች ለትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።