ነጋዴዎች እና ባለሃብቶ መፈናቀላቸው ሊቆም እንደሚገባ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት አሳሰቡ።

30

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንግዱ ማኅበረሰብ እና ከባለሃብቶች ጋር ሰላምን በዘላቂነት መፍታት ዓላማው ያደረገ ውይይት አካሂዷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦቱ በንግድ እንቅስቃሴያቸው እና አጠቃላይ በሕይዎታቸው ላይ ፈተና እንደኾነባቸው በአጽንኦት አንስተዋል። ነጋዴው እና ባለሃብቱ በየመንገዱ እና በሥራ ቦታ ላይ ንብረቱ እየወደመበት እና እየከሰረበት ይገኛል ብለዋል ተሳታፊዎቹ። ዘላቂ ሰላምን እንደሚሹም ተናግረዋል።

የሰላም አለመኖር ነጋዴውን ማኅበረሰብ እና ባለሃብቱን ከማንም በላይ እየጎዳው እንደኾነም በውይይቱ ላይ በትኩረት የተነሳ ነጥብ ነው። ወይዘሮ ዘነበች መንግሥቴ የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴ ናቸው። በየጊዜው የመንገድ መዘጋት እና በነጻነት መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ምክንያት ነጋዴዎች ለኪሳራ እየተዳረግን እንገኛለን ብለዋል።

ሰላምን ለማጥራት እያንዳንዱ ሰው የራሱን ጓዳ ማጥራት እንዳለበትም ገልጸዋል። ይህ እንዲኾን ሁሉም አካል ከመነጣጠል ይልቅ እጅ እና ጓንት ኾኖ መሥራት ግን ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ እና የሸቀጣሸቀጥ ንግድ ላይ የተሠማራችው ምሳነሽ እናናው የሰላም አለመኖር ነግደን እንዳናተርፍ እና በነጻነት እንዳንቀሳቀስ አድርጎናል ብላለች። አሁን ላይ ስለ እውነት ሰላም ናፍቆናል የምትለው ምሳነሽ ወደ ቀደመ ሰላማችን እንድንመለስ ሁላችንም ኀላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ነው ያለችው።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሴ እንደ ሕዝብ ባለፉት ጊዜያት የተከሰቱ ጥፍቶችን ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል ብለዋል። ዋጋ እያስከፈለ ያለ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን ያሉት ኀላፊዋ ካለፉ ጥፋቶች እና ችግሮች በጥልቀት መማር ይኖርብናል ነው ያሉት። ከገጠመን አስከፊ የመገዳደል እና የእርስ በእርስ የመጠላለፍ አባዜ ለመውጣት የንግዱ ማኅበረሰብ እና ባለሃብቶች ድርሻቸው ከፍተኛ ሊኾን ይገባል ብለዋል።

ባለሃብቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ በመጀመሪያ አሁን ካለው የግጭት ቀውስ ራሱን ማጽዳት ይኖርበታል፤ አለፍ ሲል ደግሞ የተከሰተው የሰላም እጦት እልባት እንዲያገኝ ኀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት። ለተቀናጀ ሁለንተናዊ ሰላም ሁሉም ያገባዋል ብለዋል ወይዘሮ ብርሃን።

በእርስ በእርስ ጦርነቱ እየደረሰ ያለው የኢኮኖሚ ድቀት ከፍተኛ እንደኾነም አንስተዋል። ሰላም ባለመኖሩ ምክንያት ነጋዴዎች በነጻነት መነገድ አልቻሉም፤ ባለሃብቶችም ማልማት ያለባቸውን ተግባር እንዳያከናውኑ አድርጓቸዋል ነው ያሉት። ለዚህ ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ታድያ ሁሉም ያገባዋልና ነጋዴዎች እና ባለሃብቶች ለዘላቂ ሰላም መጣር አለባቸው ብለዋል።

ሰላምን የሚያውኩ እና በትጥቅ ላይ ያሉትን አካላት በመመለስ በኩልም ኀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት። ንግድ እና ኢንቨስትመንት ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ሳለ ባለቤቶቹ ዝምታን መምረጥ የለባቸውም ይልቁንም የሰላም እጦቱ ሊያስጨንቃቸው ይገባል ብለዋል። “ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች ሥራቸውን ትተው መፈናቀላቸው” እና መሰደዳቸው እስከመቸ የሚለው ሊያሳስበን ይገባል ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ።

ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየከተማ ግብርና ልማት ከገቢ በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራም እያገዘ ነው።
Next articleበከለላ ወረዳ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።