የከተማ ግብርና ልማት ከገቢ በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራም እያገዘ ነው።

126

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር የከተማ ግብርና ልማት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ለአማራ ክልል የከተማ ግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥቷል። በአማራ ክልል ለስምንት ከተሞች የከተማ ግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች በከተማ ግብርና ላይ ሥልጠና እና የልምድ ተሞክሮ ልውውጥ ተደርጓል።

በግብርና ሚኒስቴር የከተማ ግብርና መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ስለሺ በቀለ ለክልል ተጠሪ በኾኑ ስምንት ከተሞች የከተማ ግብርናን ለማስፋት እና ለማሳደግ የሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም የክልሉ ግብርና ቢሮ፣ የከተማ አሥተዳደሮች የግብር መሪዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የከተማ ግብርና ማለት በከተማ አሥተዳደር ክልል ውስጥ የግብርና ልማት መሥራት ነው ያሉት አቶ ስለሺ እንደ ሥነ ምህዳሩ ሁኔታ በእንስሳት፣ በዕጽዋት እና አትክልት ብሎም በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አቶ ስለሺ የከተማ ግብርና በከተማ ውስጥ የሚገኘውን ሃብት በመጠቀም ከመሥራት በተጨማሪ ከከተማ ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር የማስዋብ ዓላማ ጭምር እንዳለው ነው የተናገሩት።

ከምግብ እና የምጣኔ ሃብት ጠቀሜታው በተጨማሪ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ከተማን የማስዋብ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል። ከኮሪደር ልማት ጋርም እንደሚመጋገብ ጠቅሰዋል። በልምድ ልውውጡም በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በዓሣ እና በእንስሳት ዘርፍ የተሠሩትን ውጤታማ ሥራዎች በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ ተደርጓል ብለዋል። በሌሎች ከተሞችም በተመሳሳይ መሠራቱን ነው የጠቀሱት።

በአዲሱ የግብርና ፖሊሲ ውስጥ የከተማ ግብርና ትኩረት አግኝቶ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶለት ሥልጠና እየተሰጠ ነው፤ በቀጣይም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የኤክስቴንሽን ሥርዓቱን እንተገብራለን ብለዋል። ፓኬጆችም ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እንገባለን ነው ያሉት። የከተማ ግብርና ከማምረት እስከ መጠቀም የሚደርስ ነው ያሉት አቶ ስለሺ በቀጣይም ሥራው በመላ ሀገሪቱ ተስፋፍቶ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አምሳሉ ጎባው የከተማ ግብርና የሥራ ባህርይ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይኾን በተለያዩ ምርቶች የተለያዩ ተቋማት የሚሳተፉበት መኾኑን አንስተው በጋራ፣ በመቀናጀት እና በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል። የከተማ ግብርና ከተሜው ባለው ምቹ ሁኔታ ምግቡን በጓሮው እና አካባቢው በማምረት የምግብ ዋስትናውን የማረጋገጫ አካል እና በአነስተኛ ቦታ ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት መኾኑን አንስተዋል።

የተጎበኘው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የዶሮ፣ የዓሣ፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ልማት ተቀናጅተው የሚሠሩበት የምርት አይነት ሲኾን በስምንት ከተሞችም እንዲሰፋ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። አዲሱ የግብርና ፖሊሲ ባለሀብቶች በከተማ ግብርና ላይም እንዲሰማሩ የሚያበረታታ መኾኑን የጠቀሱት አቶ አምሳሉ የከተማ ግብርናው የሥራ ዕድልንም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የገጠሩ እና የከተማው አሠራር በግብርናው ዘርፍ ሁለንተናዊ ትብብር በማድረግ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት። ሚዲያውም መረጃውን ለሕዝብ በማድረስ እና ተሞክሮውን በማስፋት እገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እርባታ፣ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ቡድን መሪ በለጠ መኳንንት በሥልጠናው እና በጉብኝቱ ለሥራው መነሳሳት እና መነቃቃት ተፈጥሮልናል ብለዋል። የሌሎች ሀገራትንም ተሞክሮ በማንሳት የከተማ ግብርና ያለውን አቅም መገንዘባቸውን ነው ያብራሩት።

የጽሕፈት ቤታቸው የከተማ ግብርና ሥራዎች በመልካም አፈጻጸም መጎብኘታቸው እንዳነቃቃቸው ገልጸው ”እኛ ግን ገና ብዙ መሥራት እንዳለብን ነው የምናስበው” ብለዋል። ዓሣ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ዶሮ ልማትን ከካፍቴሪያ እና ከመዝናኛዎች ጋር አስተሳስረን ለመሥራት ሰፊ ዕቅድ ይዘናልም ነው ያሉት።

ሥራው በተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳይቆም አስቀድመን አውቀን የወቅቱን የሀገር እና የወገንን ችግር ለመቅረፍ እንሠራለን፤ ችግሮች ቢገጥሙን እንኳ በቁርጠኝነት ለመጋፈጥ ተነሳስተናል ነው ያሉት። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አባይነሽ ፍስሐ በሥልጠና እና ጉብኝቱ በከተማ ግብርናው ተመጋጋቢ የኾኑ የግብርና ሥራዎችን በመሥራት ውጤታማ መኾን እንደሚቻል መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

በጉብኝታቸውም አንዱ ዘርፍ ለአንደኛው በመመጋገብ የሚመጋገቡ የከተማ ግብርናዎችን ማየታቸውንም ተናግረዋል። ወይዘሮ አባይነሽ ሴቶችን ጨምሮ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ በጠባብ መሬቶች ላይ ውጤታማ ሥራዎች መሥራት እንደሚቻል መገንዘባቸውንም ነው የገለጹት።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleወጣቶች ውይይትን በማስቀደም ከጥፋት ተልዕኮ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል።
Next articleነጋዴዎች እና ባለሃብቶ መፈናቀላቸው ሊቆም እንደሚገባ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት አሳሰቡ።