ወጣቶች ውይይትን በማስቀደም ከጥፋት ተልዕኮ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል።

12

ጎንደር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦቱን ተከትሎ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት አካሂዷል። ሰላምን ለማጽናት ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ ውይይት መደረጉን የተናገሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ብርሃኑ ናቸው።

የሰላም እጦቱ በወጣቶች እና ሴቶች ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በርካታ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ፣ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳይኾኑ፣ ሴቶች ለከፋ ሕይዎት እንዲጋለጡ ማድረጉንም አንስተዋል። ግጭት በሕይዎት ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመገንዘብ ወጣቶች ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጡ እና ሰላምን ሊያጸኑ እንደሚገባም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማሩ ሙሐመድ አሳስበዋል።

ወጣቶች ውይይትን በማስቀደም ከጥፋት ተልዕኮ ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባም አንስተዋል። የአካባቢያቸውን ሰላም በማጽናት ለሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል። የሰላም እጦቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን እያስከተለ እንደሚገኝ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች ተናግረዋል። መንግሥት ሰላምን ለማጽናት አበክሮ እንዲሠራ የጠየቁት ወጣቶቹ ሰላምን ለማጽናት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ነው ያረጋገጡት።

ሰላምን በማጽናት የጎንደር ከተማን የልማት እንቅስቃሴ ማስቀጠል እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- መሠረት ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሁሉን አካታች ለኾነው የኢትዮጵያ ዕድገት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ድርሻ አለው” ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ
Next articleየከተማ ግብርና ልማት ከገቢ በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራም እያገዘ ነው።