“ሁሉን አካታች ለኾነው የኢትዮጵያ ዕድገት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ድርሻ አለው” ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

15

አዲስ አበባ: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የኾነው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ “ኢቴክስ 2025” በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል። የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በመድረኩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ደኅንነቱ የተጠበቀ መረጃ እና የዲጂታል ዳታ ባለቤት ለመኾን የመረጃ ቴክኖሎጂ ወሳኝነት አለው።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሥራዎችን እየሠራች እና በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመኾኑም አስረድተዋል። ፕሬዝዳንቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ መረጃ እና ዲጂታል ዳታ ባለቤት ለመኾን የመረጃ ቴክኖሎጂ ወሳኝ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት። የመረጃ ደኅንነትን ለመጠበቅ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲኹም ጥራት ያለው አገልግሎትን ለማቅረብ ዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጭ ሳይኾን ግዴታ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ለቀጣይ ትውልድ የምትኾን ሀገርን ለማቆየት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን የመሰሉ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በራሳችን ኹኔታ መጠቀም አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ይህ ደግሞ ከአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ጋር የሚሄድ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትመኘውን ዕድገት እውን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለዚህ ደግሞ ዲጂታል ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና አለው፤ በዚህ ረገድም ከኤክስፖው ትልቅ ተሞክሮ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየፍትሕ ሥርዓቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next articleወጣቶች ውይይትን በማስቀደም ከጥፋት ተልዕኮ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል።