የፍትሕ ሥርዓቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

9

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሕግ ትምህርት ቤቶች በጋራ ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም የሕግ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ እና በክልሉ የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው።

በተለይም ደግሞ የአሠራር ሥርዓቶችን፣ አደረጃጀቶችን እና የሕግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል ከሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በትብብር መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። በቀጣይ የፍትሕ ተቋማትን የሰው ኀይል አቅም መገንባት የመጀመሪያ ሥራ መኾኑንም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች በንድፈ ሀሳብ የሚሰጡትን ትምህርት በተግባር እንዲደገፉ ከፍትሕ ተቋማት እና ከሕግ ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩም ነው ያስገነዘቡት።

በሕግ ምርምር፣ በጥናት እና በረጅም ብሎም በአጫጭር ሥልጠናዎች እና በአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓት ላይ በጋራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መውጣቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ከሚሠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።

የፍርድ ቤት አሥማሚነት፣ የግልግል ዳኝነት፣ ዜጎች ያለምንም እንግልት ባሉበት ኾነው እንዲገለገሉ ዲጅታላይዜሽን ላይ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር እንደሚሠራም አስረድተዋል። በቀጣይ ከሕግ ባሻገር በሌሎች መሥኮችም በጋራ የሚሠራ ይኾናል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሕጻናት ከትምህርት ገበታ መራቃቸው በቀጣዩ የትምህርት ሕይወታቸው ላይ ጠባሳ ጥሎ ማለፍ ነው።
Next article“ሁሉን አካታች ለኾነው የኢትዮጵያ ዕድገት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ድርሻ አለው” ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ