
ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ኮሌጅ 42ኛውን ዓለም አቀፍ የትምህርት ጉባኤ እያካሄደ ነው። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ኮሌጅ በየዓመቱ የትምህርት ጉባኤ ያዘጋጃል። በጉባኤው የትምህርት ሥራን የሚያሻሽሉ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችም በምሁራን እየቀረቡ ምክክር ይደረግበታል።
ጉባኤውን የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥናት እና ማኅበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር እንየው አድጎ ይህ ጉባኤ ሳይቋረጥ በየዓመቱ መካሄዱ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት እና የተግባር ሥራ ያሳያል ብለዋል። የዘንድሮው ጉባኤ በተለይም በችግር ውስጥ ኾኖም ሕዝብን ቀጣይነት ላለው ዕድገት የሚያበቃ ጥራት ያለው ትምህርት ማቅረብ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ያተኮረ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ትምህርት በግጭት ውስጥ ኾኖም እንዴት መቀጠል እንዳለበት፣ ከግጭት በኃላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በምን መልኩ መሠራት እንዳለበት በጉባኤው ላይ ውይይት ይደረግበታልም ብለዋል ፕሮፌሰር እንየው። በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዓለም አቀፍ የትምህርት ልማት ከፍተኛ ባለሙያው ጣሰው ዘውዴ(ዶ.ር) የትምህርት ጥራትን የሚያጓድሉ ኹኔታዎች፣ የትምህርት ጥራት መጓደል በሕዝብ እና በሀገር ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ እና ችግሩን ለመፍታት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች አንስተዋል።
ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ከኾኑ ጉዳዮች ውስጥ የመምህራን ብቃት፣ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ብዛት እና ጥራት፣ የትምህርት ቤት አካባቢዎች ሰላም መኾን እና ሌሎችም ተነስተዋል። በተለይም የሰላም ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የትምህርት ሥራ በሰፊው እንደሚጎዳ ተነግሯል። በግጭት ውስጥ ኾኖም ትምህርት ሊቆም የማይገባው መሠረታዊ ነገር ስለመኾኑም ተገልጿል።
“ትምህርት ቆመ ማለት ለወደፊት የምንመኘውን ነገር ሁሉ ትተን ወደኃላ መመለስ እንደማለት ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ሕጻናት የቋንቋ ትምህርታቸውን የሚጨብጡት በለጋ የልጅነት ጊዜያቸው እንደኾነ የጠቆሙት ዶክተር ጣሰው በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከትምህርት ገበታ መራቃቸው በቀጣዩ የትምህርት ሕይወታቸው ላይም ጠባሳ ጥሎ እንደሚያልፍ አመላክተዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን ትምህርት ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል። በግጭት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንደገና ለመቀጠል ዝግጁ መኾን፣ መምህራን በቶሎ ወደ ትምህርት ቤት መመለስ፣ ተማሪዎችን በሥነ ልቦና መደገፍ፣ እና ፈጥኖ ትምህርት መጀመር፣ ከተጀመረ በኃላም በመተባበር መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተለይም በአማራ ክልል ሕጻናት ለሁለት ዓመታት ያህል ከትምህርት ገበታ ተለይተዋል፤ ይህም ከዕድሜያቸው ላይ እንደመቀነስ ይቆጠራል ነው ያሉት። ትምህርት የሕይወት ጉዳይ በመኾኑ ሁሉም በጋራ እና በትብብር ሊሠራበት የሚገባ እንደኾነም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሌሎች ትምህርትን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችም በጉባኤው ላይ ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን