
አዲስ አበባ: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ በአዲስ ዓለም ኦፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተገልጿል። ከ10ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት እና በምሥራቅ አፍሪካ በአይነቱ ትልቅ የኾነ ዓለምአቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ነው በአዲስ አበባ የሚካሄደው።
“ኢቴክስ 2025” ኤክስፖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያተረፉ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የቴክኖሎጂ ኤክስፖም ነው። በኤክስፖው ከፍተኛ ተቀባይነት እና ዕውቅና ያላቸው ከመቶ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
ኤክስፖውን ያዘጋጁት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሳይበር ደኅንነት ተቋም ጋር በመተባበር ነው። የሳይበር ደኅንነት፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ስማርቲ ሲቲ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ጨምሮ የሮቦቲክስ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውድድሮችም የሚካሄዱበት ነው።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን