
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር ለማኅበረሰባችን ጥራቱን የጠበቀ እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ የኅብረተሰቡን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መኾኑ የዓደባባይ ሃቅ ነው።
ምክንያቱም መቼም እና በምንም ሁኔታ መቋረጥ ከሌለባቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች አንዱ የጤና አገልግሎት በመኾኑ፤ ስለዚህም ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ቀናት በመላ ሀገራችን በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደ ወትሮው ሁሉ መደበኛ የጤና አገልግሎቶች ለማኅበረሰባችን ያለምንም መቆራረጥ እና መስተጓጎል እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡
ይሄንን የተረዳው የጤና ባለሞያ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሠራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ጫና ሳይገፋ የገባውን የሞያ ቃል ኪዳን እና መሐላ ጠብቆ ማኅበረሰቡን እያገለገለ በመኾኑ ምስጋና ይገባዋል፡፡
ይሁን እንጂ በጥቂት የማስተማሪያ የጤና ኮሌጆች (ተቋማት) በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ የተወሰኑ ባለሞያዎች እንዳሉ መረጃዎች ደርሰውናል፡፡ ከእነዚህ የጤና ባለሞያዎች መካከል ብዙዎቹ በሃሰተኛ መረጃ የተወናበዱ ሲኾኑ ጥቂቶቹ ደግሞ ጥፋትን ዓላማቸው ያደረጉ ናቸው።
ድርጊቱ የራስን ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወገን እና መላውን ማኅበረሰብ ከመጉዳት ባለፈ ከሞያ ሥነ ምግባር፣ ከሰብዓዊነት አኳያ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው።
ከሕግ አኳያም የጤና ሞያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መኾኑ በግልጽ ተደንግጓል። የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ እንኳን ቢኖራቸው በሥራ ገበታቸው ተገኝተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በመኾኑም እነዚህ የጤና ባለሞያዎች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ በየተቋማቸው ጥሪ ተደርጓል።
መንግሥት የጤና ባለሞያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ቀደም ብሎ የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1362 /2017 አጸድቆ ደንብ እና መመሪያዎችን በማውጣት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
በጎ ኅሊና ያላቸው የጤና ባለሞያዎች ይህንን በመገንዘብ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሠራጩ የሐሰት መረጃዎች ሳይረበሽ የሚፈልገውን የጤና አገልግሎት በተለመደው መልኩ በጤና ተቋማት ማግኘት እንደሚችል እናሳውቃለን።
መንግሥት በሆደ ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ትዕግሥት ወደጎን በመተው በሥራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ እንዲሁም በጤና ተቋሙም ኾነ ከጤና ተቋሙ ውጭ ኾነው ሁከት እና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ አስፈላጊ የኾነ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መኾኑን ቀድመን እናሳውቃለን፡፡
የጤና ሚኒስቴር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!