በዲጂታል ዘመን የሚዲያ ሰዎች ለእውነት በመቆም ሀገርን የማሻገር ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

29

ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሚና እና የቀጣይ አቅጣጫ” በሚል መሪ መልዕክት ከማኀበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና ከኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርጓል፡፡

የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የኾኑት አልታሰብ አስፋው ሀገር የጋራ ስለኾነች ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ስትሄድ ትክክል አይደለም ብሎ መናገር እና መገሰጽ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ስለኾነም ሀገሪቱ ከገባችበት ሁለንተናዊ ቅርቃር ለማውጣት ከሚዲያዎች ብዙ አዎንታዊ ነገሮች ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች ሀገር ከገባችበት ችግር እንድትወጣ ከመሥራት ይልቅ ግላዊ ጥቅማቸውን ለማሟላት ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ያልተገባ አስተሳሰብን በማራመድ እና ግጭትን በማራገብ ብሎም በማስፋፋት ሀገርን በሁለንተናዊ መንገድ ይጎዳሉ ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል ያለው ነባራዊ ሐቅ እንዲወጣ አንቂዎች እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ከፍተኛ ሥራ ማከናዎናቸውን አቶ አልታሰብ ተናግረዋል፡፡ ለአብነት ባሕር ዳር ከተማ ”ሰላም አይደለችም ብለው ለሚያሟርቱባት ግጭት ጠማቂዎች” ከተማዋ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ መኾኗን እና እያሳለጠች ያለውን ልማት በሌሎች አካባቢዎች ለሚኖሩ ወገኖች እውነቱን እየነገሩ ያሉት ቀናኢ ሚዲያዎች እና አንቂዎች ናቸው ብለዋል፡፡

አንዳንድ አንቂዎች እና ሚዲያዎች እየሄዱበት ያለው አቅጣጫ ጥሩ አይደለም ያሉት አቶ አልታሰብ ሀገር ከሌለ ማንም መኖር አይችልም፡፡ ስለኾነም ሀገር እንድትረጋጋ ከማኀበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ከኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እና ከኅብረተሰቡ ብዙ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያ ኀይሌ ዘውዱ ደግሞ ሚዲያ ለአንድ ሀገር ግንባታ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሁሉም አንቂዎች እውነታን ይዘው ትውልድ እንዲሻገር እና ሀገር ሰላም እንድትኾን ከአንቂዎች ብዙ በጎ ሥራ ይጠበቃል፡፡

አባቶቻችን እና እናቶቻችን ዓድዋ ላይ ታሪክ ሠርተዋል ያሉት አቶ ኀይሌ እኛም አዲስ ታሪክ በመሥራት ለልጆቻችን ሰላማዊ ሀገርን ለማስረከብ ሁሉንም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ታምራት አሻግሬ በከተማዋ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም እንዲጸና እና የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እና ከማኅበራዊ አንቂዎች በርካታ ሥራዎች ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የአማራ ክልል በርካታ ችግሮችን ማለፉን አስታውሰዋል፡፡ ሰላምን እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዴት መዝለቅ እንዳለባቸው ሰፊ ሥራ ተከናውኗል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ቤተሰቦች ሀገር በማረጋጋት፣ እውነትን በመንገር ሕዝብ የሚያሸብረውን በማጋለጥ፣ ሕዝብን ለበጎ ሥራ በማነሳሳት ረገድ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በዲጂታል ዘመን የሚዲያ ሰዎች ለእውነት በመቆም ሀገር በማሻገር ዋነኛ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአማራ ክልል የኩፍኝ በሽታ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ ነው።
Next articleበወቅታዊ የጤና አገልግሎት ዙሪያ ከጤና ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ፦