
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ3 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የኩፍኝ በሽታ ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝ ጤና ቢሮ ገልጿል። ክትባቱ ከግንቦት 06/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ነው። እስከ ግንቦት 15 /2017 ዓ.ም ድረስ በዘመቻ መልክ በክልሉ ባሉ 175 ወረዳዎች እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ክፍል አሥተባባሪ ተሰማ በሬ ተናግረዋል፡፡
የኩፍኝ በሽታ በቫይረስ አማካኝ ነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በትንፋሽ እና ከመተንፈሻ አካል ጋር ተያይዞ በሚመጡ ፈሳሾች ከበሽተኛ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው የሚተላለፍ እና ለአይነ ስውርነት፣ ለጀሮ ሕመም አለያም ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ ወይዘሮ እናት ደስታው በባሕርዳር ከተማ ሽምብጥ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ ልጃቸውን ሲያሰከትቡ ነው ያገኘናቸው፡፡ የሁለት ልጆች እናት የኾኑት ወይዘሮዋ የመጀመሪያ ልጃቸው የስድስት ዓመት ልጅ መኾኑን በመግለጽ እስከ አምስት ዓመቱ ድረስ በመንግሥት በኩል የሚመጡ ማንኛውንም የክትባት አይነቶች ማስከተባቸውን ነግረውናል፡፡
ዛሬም የአርባ ሁለት ቀን አራስ ልጃቸውን ክትባት ሊያሰጡ መምጣታቸውን በመግለጽ በቀጣይም የሚመጡ ክትባቶችን በመከታተል እንደሚያስከትቡ ነው የተናገሩ፡፡ ክትባቱ ልጆቻቸውን ከተለያዩ ተላላፊ እና ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች ይጠብቅልኛልም ነው ያሉት፡፡ ሌላኛዋ ልጃቸውን ሲያስከትቡ ያገኘናቸው እናት ወይዘሮ አብነት ተስፋ ይባላሉ፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ እርሳቸውም የዘጠና ቀን እና የሁለት ዓመት ልጆቻቸውን ሊያስከትቡ መምጣታቸውን ነው የነገሩን፡፡
ክትባቱ ልጆቸን ከኩፍኝም ኾነ ከሌሎች ወረርሽኝ በሽታዎች ስለሚታደግልኝ ምንጊዜም ተከታትየ አስከትባቸዋለሁ ነው ያሉን፡፡ ያለምንም ወጭ በነጻ ለሚደረግልኝ ግልጋሎት ምሥጋናየን አቀርባለሁ ያሉት ወይዘሮ አብነት ሌሎች እናቶችም ይህንን ዕድል በመጠቀም ልጆቻቸውን ከበሽታ ሊጠብቁ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሽታው ክትባቱን ያልወሰደ ወይም በተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም የሌላቸው ማንኛውንም አይነት የኅብረተሰብ ክፍልን ያጠቃል፤ በተለይ ደግሞ አምስት ዓመት እና ከዛ በታች ያሉ ሕጻናትን በዋናነት እንደሚያጠቃ የተናገሩት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት አሥተባባሪ ተሰማ በሬ ናቸው፡፡
በዚህ ምክንያትም የክትባት ዘመቻው መርሐ ግብር አምስት ዓመት እና ከዛ በታች ላሉ ሕጻናት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡ ይህ የኩፍኝ በሽታ ክትባት በአዲስ መልክ የሚሰጥ አይደለም ያሉት አሥተባባሪው ክትባቱ በሀገራችን ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ከመደበኛ ክትባቶች አንዱ ኾኖ ሲሰጥ የቆየ የክትባት አይነት ነው ብለዋል፡፡
አኹንም ከግንቦት 6/2017 እስከ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም ድረስ በሚደረገው የኩፍኝ በሽታ የክትባት ዘመቻ በአማራ ክልል 3 ሚሊዮን 749 ሽህ 171 ከዘጠኝ ወር እስከ 59 ወር ላሉ ሕጻናት ይሰጣል ተብሎ በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ካሉ 175 ወረዳዎች 165 ወረዳዎች ወደ ክትባት ዘመቻው ገብተዋል፡፡
በዘመቻ የሚሰጡ ክትባቶች በመደበኛ የሚሰጡ ክትባቶች ማጠናከሪያ በመኾናቸው በመደበኛ የተከተቡም ኾነ ያልተከተቡ ሕጻናት በዘመቻ የሚሰጡ ክትባቶችን ሊወስዱ ይገባል ያሉት አሥተባባሪው ይህም ክትባቱ ለሕጻናት እንደ ተጨማሪ ዕድል ነው ብለዋል፡፡
የክትባት ዘመቻው በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲኾን ለማኅበረሰቡ ዕውቅና ለመፍጠር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን በማስታወስ በአንዳንድ አጋጣሚዎች መረጃውን ባለማግኘት ሕጻናት ክትባቱን ሳያገኙ እንዳይቀሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአካባቢያቸው ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማሳወቅ እና እንዲከተቡ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በክትባት ዘመቻው ወቅትም ጎን ለጎን ክትባት ያልጀመሩ ሕጻናት ክትባት እንዲጀምሩ ይደረጋል፣ አጣዳፊ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሕጻናትን የመለየት እና ሕክምና የመስጠት ሥራ ይሠራል፣ ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት ላሉት የቪታሚን ኤ ጠብታ እና የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድኃኒት ይሰጣል፣ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሽንት እና ሰገራ መቆጣጠሪያ ችግር ያለባቸውን ሰዎች የመለየት እና ወደ ሕክምና የመላክ፣ በተፈጥሮ የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ የገጠማቸውን ልጆች በመለየት ወደ ሕክምና የመላክ፣ በተፈጥሮ የተጣመመ እግር ያላቸውን ሕጻናት የመለየት እና ወደ ሕክምና የመላክ ሥራም ይሠራል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን