
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) እና ልዑካቸው ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያልተቋጩ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ እና የተዛባ ግንዛቤ የነበረባቸውን ጉዳዮች ማጥራት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ፣ የግድቡ የደኅንነት ሁኔታ እና የመረጃ ልውውጥን ስለ ማመቻቸት፣ በሱዳን በኩል ለተነሡት ጉዳዮች ምላሽ እንደተሰጠባቸው ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡
ወቅታዊ የሥራ ክንውኑ ያለበትን ደረጃ ደግሞ ዶክተር ዐቢይ ገልጸውላቸዋል። በማብራሪያቸውም የሕዳሴው ግድብ ለሦስቱ የተፋሰሱ ሀገራት ኢኮኖሚ መጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
የቴክኒክ ውይይቱንም በሁለቱ ሀገራት የውኃ ሚኒስትሮች አማካኝነት ለመቀጠል እንደተስማሙ ነው የተገለጸው፡፡