የሰላም አማራጭን ለሚከተሉ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል በትኩረት እየሠራ መኾኑን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ገለጸ።

22

ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በአማራ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚያስችልበት ጉዳይ ዙሪያ ከክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ምክክር አድርጓል። የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልልም ከጥር/2017 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥትን እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎችን ወደ ሥልጠና ማዕከላት በማስገባት እና ድጋፍ በማድረግ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ገልጸዋል። በክልሉ አሁንም ግጭቶች በመኖራቸው የሰላም አማራጭን ለሚከተሉ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

እስከ አሁን ኮሚሽኑ በሠራው ሥራ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ በቀጣይም ሰላምን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ ከክልሉ መንግሥት ባለፈ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ማኅበረሰቡም ታጣቂዎች ጥያቄዎቻቸውን በሰላም እንዲያቀርቡ የድርሻውን እንዲወጣ ነው ያሳሰቡት። ሰላምን መርጠው ወደ ማኅበረሰቡ ለሚቀላቀሉት ደግሞ ማገዝ ይገባል ብለዋል።

ታጣቂዎችም ሰላማዊ አማራጭን በመከተል የሚሰጠውን ተሐድሶ በመውሰድ የልማት አቅም እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል። ሰላምን መርጠው ወደ ማዕከላት ለሚገቡት ደግሞ ኮሚሽኑ የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየገጠር መንገድ ትስስር እና ተደራሽነት ፕሮጀክትን በስኬታማነት ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
Next articleበአማራ ክልል የኩፍኝ በሽታ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ ነው።