
አዲስ አበባ: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር መንገድ ትስስር እና ተደራሽ ፕሮጀክትን በስኬታማነት ለመተግበር የሚያስችል ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። የመግባቢያ ሥምምነቱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥት ግዥ እና ንብረት ባለሥልጣን፣ የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የኮንስትራክሽን ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ሄልቤታስ ኢትዮጵያ ተፈራርመውታል።
የሥምምነቱ ዋና ዓላማ ከእነዚህ ተቋማት ጋር ፕሮጀክቱን በስኬታማነት ለመተግበር እና በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል መኾኑ ነው የተገለጸው። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ድኤታ የትምጌታ አስራት እንደ ሀገር በቂ እና ምቹ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረጉ መኾኑን አንስተዋል።
የገጠር መንገድን ከዋና መንገዶች ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል በመንግሥት እና በዓለም ባንክ በተገኘ የ407 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። ፍትሐዊ እና አካታች የኾነ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በሁሉም የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ተደራሸ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ነው፤ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማም የገጠር መንገድን ከዋና መንገድ ጋር ማስተሳሰር እና የመንገድ ተደራሽነትን ማስፋት ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር የገጠር መንገዶችን ከዋና መንገዶች የሚያገናኙ በቂ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴያዎች ማፋጠን የፕሮጀክቱ ተቀዳሚ ዓላማ መኾኑንም አስረድተዋል። ይህ ፕሮጀክት በመንግሥት የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅዶች ከተካተቱ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ መኾኑን ነው የገለጹት።
እንደ ሀገር አሁን ላይ ያሉት የመንገድ አውታሮች መጠን 171 ሺህ ኪሎ ሜትር ነው። በዚህ ፕሮጀክት ከ7ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስ የገጠር መንገድ ግንባታ፣ 700 ኪሎ ሜትር በላይ መሻገሪያ ኮንክሪት ድልድዮች፣ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የተንጠልጣይ ድልድዮች እና ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገዶች ጥገና ይደረጋል ብለዋል።
በአብዛኛው ቆላማ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን የመንገድ ይገንባልን ጥያቄም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መኾኑን አንስተዋል። የታቀዱ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በታለመላቸው ጊዜ፣ በጀት እና ጥራት እንዲገነቡ የተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰዋል። እነዚህ ተቋማት በሀገራዊ ኀላፊነት እና በታማኝነት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የተቋማት ተወካዮችም ፕሮጀክቱ በስኬታማነት እንዲተገበር ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እና በታማኝነት እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን