
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከተሞችን ዘመናዊ (ስማርት ) በማድረግ ሂደት የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የትራንስፖርት ሥርዓት፣ የኃይል አማራጭ እና ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎቶች ዋና መዋቅሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቁልፍ መዋቅሮች ውስጥ የዲጂታል መሠረተ ልማት የምንለው የነገራተ ኢንተርኔት (IoT) መሳሪያዎች፣ ፈጣን ኢንተርኔት እና የመረጃ ትንተና ሥርዓት አቀናጅቶ የያዘ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሞችን የማዘመን እና የማስዋብ ሥራ በአብዛኞቹ የሀገራችን ከተሞች እየተገበረ ይገኛል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አካል የኾነው የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የዝማኔ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ ለውጥን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ ባሕር ዳርን በማስዋብ እና በማዘመን ሂደት በዙር ተከፍለው ሥራዎች እየተሠሩ ሲኾን በመጀመሪያ ዙር የስማርት ፖል ዝርጋታ አማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በራስ አቅም የተመረቱ ምሰሶዎች በዚህ ምዕራፍ እንዲሸፈኑ በዕቅድ የተያዙ አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ተግባራዊ የተደረጉ ምሰሶዎች ባሕር ዳርን ስማርት ለማድረግ ከተጀመሩ ተግባራት አንዱ መኾኑን የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ አስረድቷል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የተተከሉት ብላክ ስማርት ምሰሶዎች ከሰባት በላይ ዘመናዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በውስጡ ያካተተ መኾኑን በአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የመገጣጠም እና የማጠናቀቅ ሥራዎችን የሚያሥተባብሩት አቶ እንዳለው አድማሱ ተናግረዋል።
በባለ ገመድ እና ገመድ አልባ አማራጭ ቻርጅ ማድረጊያ፣ ሦስት የተለያዩ ቀለማትን በፕሮግራም እያፈራረቀ የሚያበራ የመብራት ሥርዓት፣ በበዓላት እና የእረፍት ቀናት ነዋሪዎችን በሙዚቃ ለማዝናናት የሚያስችል የድምፅ ማጉያ፣ ፕሮግራሞችን፣ መልዕክቶችን እና ማስታዎቂያዎችን ለማሳየት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ደብል ስክሪን ያለው ትዕይንተ መስኮት እና 360 ዲግሪ እየተሽከረከረ እስከ 300 ሜትር ራዲየስ የሚቀርጽ ካሜራ ያካተተ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ በተቋሙ የመገጣጠም እና የማጠናቀቅ ሥራ ክፍል ኀላፊ የኾኑት ይነበብ ታምሩ በበኩላቸው ምሰሶዎቹ የተገጠመላቸው ቴክኖሎጂዎች አደጋ በሚያጋጥማቸው ጊዜ ችግር መኖሩን የሚጠቁም ማንቂያ ያላቸው በራስ አቅም ሥራ ላይ የዋሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ ለምርምር አገልግሎት የሚውሉ የትራፊክ እና የአየር ሁኔታ መረጃን ማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን