
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ”ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ መልዕክት ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በመድረኩ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ጨምሮ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዱር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ መሪዎች እና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች እና አማተር ከያኒያን ተሳትፈዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ኪነ ጥበብ ለሀገር ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። ይህንን አቅም ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ልማት እና ችግሮችን ለመፍታት ከኪነጥበብ ሰዎች ጋር ፖሊሲ ተኮር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል።
ኪነ ጥበብን ለሀገር ግንባታ ዓላማ በውል ለመጠቀም ከከያኒያን ጋር ምክክር ማድረግ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። ዘርፉም ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ ሚና ቢጫዎትም ማደግ የሚገባውን ያህል አለማደጉንም አንስተዋል። ባልተመቸ ኹኔታ ውስጥም ኾነው ሙያቸውን ለሀገር ግንባታ እና ለኪነጥበብ ኢንዱስትሪው ማደግ ያዋሉ ከያኒያን እንዳሉም አስረድተዋል።
ለኪነ ጥበብ ይሰጥ የነበረውን ትኩረት ከፍ እና ዝቅ ማለት አንስተው ይህንን የትኩረት ማነስ በማስተካከል የዘርፉን አቅም ለሀገረ ልማት መጠቀም ማስፈለጉንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ኪነ ጥበብ ትውልድን ለማነጽ እና ለሀገር ግንባታ ያለውን ከፍተኛ አቅም አንስተዋል።
አሜሪካን ካገዘፏት መካከል ሆሊውድ አንዱ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር አየለ በኪነ ጥበብ ሥራ ሀገራት እንደሚሠሩ እና እንደሚገዝፉ ገልጸዋል። በችግር ጊዜም ኾነ በድሎት ኪነ ጥበብ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። የኪነ ጥበብ ሰዎችም አርቆ ተመልካች፣ መፍትሄ አመላካች፣ እያዝናኑ መልዕክት የሚያስተላልፉ እና ለለውጥ የሚተጉ ናቸው ብለዋል ዶክተር አየለ።
በኢትዮጵያም ኪነ ጥበብን በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ለዘመናት ያዝ ለቀቅ እንደነበር ጠቅሰው በአኹኑ ጊዜ ግን የኪነ ጥበብን አቅምን ለመጠቀም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ኪነ ጥበብ ለአሠባሣቢ ትርክት ለመጠቀም ሥራ ተጀምሯልም ብለዋል። የተጀመረው ውይይትም ጥበብን እና ጥበበኞችን ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ለመጠቀም የሚደረገው ሥራ አንድ አካል መኾኑንም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለኪነ ጥበብ ትኩረት መስጠቱ ለዘርፉም ትልቅ ዕድል ነው። በዚህ ዕድልም ባለሙያዎች ለሀገርም ለሙያውም ማደግ ጠቃሚ ሀሳብ በማዋጣት አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ነው ያሉት። በየደረጃው በሚገኙ የውይይት መድረኮች ላይም የሙያው ሰዎች ሀሳባቸውን እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን