“የፋይናንስ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የፋይናንስ ተቋማት በትብብር መሥራት እና ዘርፉን ማዘመን ይገባቸዋል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

34

አዲስ አበባ: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት፣ የግል እና ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት እየተሳተፉበት ያለው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በፎረሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በወጉ እና በሥርዓት መምራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ተግባራዊነት ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓትን መገንባት ወሳኝ መኾኑንም አስረድተዋል። በተለይ አሁን ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት ለማስቀጠል የመንግሥት፣ የግል እና ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ፣ ሀገራዊ ዕድገትን ዕውን ለማድረግ እና ከትሩፋቱም ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ እነዚህ ተግባራትን መከወን በእጅጉ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ዛሬ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፎረምም በእነዚህ አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት የሚመክር ይኾናልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ብሔራዊ ባንክ ከዓመታት በፊት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት ልምዱ ዝቅተኛ ነበር ብለዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተናጠላዊ አሠራሮች በርካታ ችግሮች ውስጥ ይገባ ነበር ነው ያሉት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ችግር እየተቀረፈ እና ከመንግሥታዊ እና የግል የፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ሥርዓቶች መገንባታቸውን አስረድተዋል። የዛሬው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፎረም ደግሞ ታሪካዊ እና ትብብራዊ ሥራን ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ብለዋል። ትብብራዊ ሥራውም የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለማስፈን የላቀ ሚናን ይጫዎታል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየማኀበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እውነትን ለሕዝብ በመንገር ሀገራዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
Next article“የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተመልሰው የልማት አቅም እንዲኾኑ የክልሉ መንግሥት ድጋፋን አጠናክሮ ይቀጥላል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ