የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ እየተሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።

10

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ በሰላም እና ጸጥታ፣ በኃይል ማሰባሰብ፣ በማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ፓኬጆች አተገባበር እና በሕግ ማስከበር ተግባራት አፈጻጸም ላይ ግምገማ እያካሄደ ነው።

የከተማ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አበበ ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት የከተማው የጸጥታ መዋቅር በተሻለ ቁመና ላይ እንደኾነ ተናግረዋል። ከሌሎች መዋቅሮች ጋር በመቀናጀትም ውጤታማ የሕግ ማስከበር ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በራስ አቅም ቀበሌዎችን ተረክቦ ሰላም የማስከበር ሥራውንም በቁርጠኝነት እያከወነ መኾኑን ጠቅሰዋል። የከተማው የጸጥታ መዋቅር አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሚሰጣቸውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ቀን ከለሊት ፈጥኖ በመፈጸም ውጤት ማስመዝገባቸውንም አቶ መኳንንት አብራርተዋል።

በዚህ ዓመትም የኃይል ማሰባሰብ ሥራዎች በትኩረት እየተሠራባቸው መኾኑን ጠቅሰዋል። በሁሉም ክፍለ ከተሞች ወጥነት ያለው እንዲኾን መሥራት ይጠበቃል ባይ ናቸው። በከተማዋ ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ማስቆምም ከጸጥታ መዋቅሩ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። የሕገ ወጥ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ፣ እገታ እና መሰል ወንጀሎችን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም እና ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብም በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ተግባር መግባት ከጸጥታ መዋቅሩ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በመድረኩ በቢሮ ኀላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይን ጨምሮ የከተማ አሥተዳደሩ የጸጥታ መዋቅር ኀላፊዎች እና አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ: ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምስጋና አቀረበች።
Next articleየማኀበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እውነትን ለሕዝብ በመንገር ሀገራዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።