
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በውጭ ሀገር ይኖሩ የነበሩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል። ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጰሳት አዲስ አበባ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር መግባታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግጫውም በውጭ አሕጉረ ስብከት ተመድበው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በመፈጸም ላይ የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር)፣ የሰሜን ካሊፎርኒያ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ.ር) እና የጆርጅያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን እንዲሳተፉ ቤተክስቲያኗ ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጿል።
መንግሥትም ሀገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት የጸና መኾኑን በገለጸበት መግለጫ እንደተመለከትነው የሀገራችንን ሰላም ለማጽናት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የታሪክ ገጽታ ለመጠበቅ ተቀራርቦ መነጋገር የተሻለ መፍትሔ መኾኑን ተረድቶ ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር ገብተው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤን እንዲሳተፉ መፍቀዱን ተረድተናል ብሏል።
መንግሥት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያቀረበችውን ጥያቄ ተቀብሎ ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር እንዲገቡ በመፍቀዱ እና ተግባራዊ ምላሽ በመስጠቱ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን ነው ያለው። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ወደ ፊትም እግዚአብሔር በሰጠን ምድር፣ አባቶቻችን ባቆዩልን ሀገር አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ለሀገራችን እና ለሕዝባችን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ግንኙነታችንን በማጠናከር በጋራ ለመሥራት ዝግጁዎች መሆናችንን እንገልጻለን ብሏል መግለጫው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን