
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንዲት ሀገር በተለይም ለግብርና አመች ለኾነች ሀገር ለኢኮኖሚዋ እድገት የግብርናው ዘርፍ የማይተካ ሚና ይጫዎታል። የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ መሠረት ኾኖ ኢንዱስትሪውን ሲያሻግር የዚያች ሀገር ትንሳኤዋ እና በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ የራሱን ሚና ይጫዎታል።
በዚህ ረገድ አሜሪካን እና ቻይናን ጨምሮ ብዙ የሚጠቀሱ ሀገራት ቢኖሩም ይህን ዘርፍ በትክክል ለሀገር መሻገሪያነት እና ትንሳኤነት በቅርቡ ከተጠቀሙ እና እንደማሳያ ከሚወሰዱ ሀገራት መካከል ብራዚል ተጠቃሽ ናት። ይህች ሀገር በግብርና ሜካናይዜሽን በተለይም በአኩሪ አተር ምርት ላይ ያሳየችው እድገት አስደናቂ ነው። ለዚህ እድገቷ ደግሞ ሜካናይዜሽን ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
የብራዚል የግብርና ዘርፍ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ቀስ በቀስ ወደ ሜካናይዜሽን እያደገ መጥቷል። ይኹን እንጂ ከፍተኛ የኾነ እድገት የታየው ከ1990ዎቹ በኋላ በተደረጉ የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና የዓለም ገበያ ፍላጎት መጨመር ነው። የብራዚል መንግሥት ለግብርና ምርምር እና ለሜካናይዜሽን ግዢ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመተግበር ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል።
የግብርና ማሽኖች አምራቾች ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን የሚያሳድጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ጂፒኤስን ያካተቱ ትራክተሮች፣ ዘር የሚተክሉ ማሽኖች እና አጫጆች በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል። በተለይም የእስያ ገበያዎች ለአኩሪ አተር ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ብራዚል ምርቷን እንድታሳድግ እና ሜካናይዜሽንን እንድትተገብር አበረታቷታል።
ይህ ሥራ ብራዚልን በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ የአኩሪ አተር አምራቾች እና ላኪዎች አንዷ እንድትኾን አስችሏታል። የአኩሪ አተር ምርት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ አስተዋጽኦ አለው። ከዚህ አኳያ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሻለ አቅም ያላት ኢትዮጵያ በቅርቡ የሜካናይዜሽን ሥራ ሀገርን እንደሚያሻግር እና ለለውጥ መሠረት እንደኾነ በማመን በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ከዚህ አንጻር ለሜካናይዜሽን የግብርና ሥራ ሰፊ አቅም ካላቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚጠቀሰው አማራ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ሰፊ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል። በክልሉ ከሚታረሰው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 42 በመቶ የሚኾነው ለግብርና ሜካናይዜሽን እርሻ የተመቸ ቢኾንም እስካኹን ግን ከ14 በመቶ በላይ ግን ማሻገር አልተቻለም።
ክልሉ ባለፉት ዓመታት ለሜካናይዜሽን ሥራ በሰጠው ትኩረት ከ220 በላይ የእርሻ ትራክተሮችን አስገብቶ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት አድርጓል። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ እንደነገሩን አማራ ክልል ያለውን አቅም ለመጠቀም እንዲችል ሜካናይዜሽን ወሳኝ እንደኾነ አምኖ እየሠራ ነው።
የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የእርሻ ሜካናይዜሽን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የማድረግ እና አሳምኖ የመሥራት ጉዳይ ላይ ስለመሠራቱም ተናግረዋል። ምንም እንኳን በሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ባይባልም በየጊዜው እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ነው የሚገልጹት። በዚህ ዓመት ሜካናይዜሽንን ለማስፋት እየተሠራ ሲኾን 980 ሄክታር መሬትን በሜካናይዜሽን እርሻ ለመሸፈን ታቅዶ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 167 ሺህ 468 ሄክታር መሬት ስለመታረሱ ተናግረዋል።
አካባቢን መሠረት ያደረገ እና እንደየ አካባቢው መሠረት ተደርጎ እና ጥናት ተደርጎ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው ዳይሬክተሯ ያብራሩት። በዚህ ዓመት ወደ ሜካናይዜሽን ሊገባ ይገባዋል የተባለን የእርሻ መሬት ከአርሶ አደሮች ጋር በተለያዩ መንገዶች በመመካከር የተበጣጠሰውን እና ለሜካናይዜሽን የማይመች የነበረውን መሬት እንዲመች የማድረግ ሥራ እንደተሠራም ጠቁመዋል።
በተለይም በተያዘው የምርት ዘመን 403 የአካባቢውን ኹኔታ ያገናዘቡ ትራክተሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተሠራም ስለመኾኑ አስገንዝበዋል። በዚህ ዓመት የሜካናይዜሽን ፍላጎት ያላቸውን አካባቢዎች ቢሮው በትኩረት እየተከታተለ ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ስለመኾኑም ነው ያረጋገጡት።
አንድም አርሶ አደር ያለፍላጎቱ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን እንደማይወስድ እና መሳሪያዎቹ የአካባቢውን የተፈጥሮ ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ ትራክተሮች እና መሰል አጋዥ መሳሪያዎች እንዲደርሱ እየተደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። የሜካናይዜሽን ሥራ የተሻለ የምርት እድገት ለማምጣት የሚሠራ በመኾኑ ይህን የማያረጋግጥ ሥራ እንደማይሠራም ነው ለአሚኮ የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን