መሰባሰቦች ቢፈቀዱ ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት ሊያጋጥም እንደሚችል ዶክተር ሊያ ታደሰ አስገነዘቡ፡፡

263

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የምርጫ መካሄድ በኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጫና ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ እያቀረቡ ነው፡፡ በማብራሪያቸውም የሰዎች መሳባሰብ አንድ ሰው በርካቶችን በቫይረሱ እንዲያስይዝ ስለሚያደርግ አደገኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ሃይማኖታዊና ስፖርታዊ መሰባሰቦች በተለያዩ ሀገራት ዋና አስፋፊ ሆነው መገኘታቸውንም ዶክተር ሊያ አስገንዝበዋል፡፡

ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ቢጠቀም ምርጫ ለማካሄድ ይቻል እንደሆነ የተጠየቁት ዶክተር ሊያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ስርጭቱን ለመከላከል አስተዋጽኦ ቢያደርግም በአካላዊ ርቀትና ሌሎችም የመከላከያ ዘዴዎች መታገዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ጥናት የሚጠይቅና ደረጃቸውን የጠበቁ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን መጠቀምን ሁሉ የሚጠይቅ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ቫይረሱ በኢትዮጵያ እንደ ሌሎች ሀገራት በፍጥነት የመጨመር ሁኔታ ያልታየበትን ምክንያት በተመለከተ ሲያስረዱም በአፍሪካ ሥርጭቱ ዘግይቶ መጀመሩንና እያደረሰ ያለው ጉዳት ገና ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በአህጉሩ የምርመራ አቅም ዝቅተኛ መሆንም በእርግጠኝነት መስፋፋቱ አነስተኛ ስለመሆኑ ለመናገር እንደማያስችል አመልክተዋል፡፡ ምልክት የማያሳዩ ታማሚዎች መኖራቸውንም ዶክተር ሊያ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያም ብዙ ሰዎች ምልክቱ ሳይታይባቸው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ነው ያመለከቱት፡፡

ምርጫ መሰባሰብን የግድ ስለሚልና የበርካታ አካላትን እንቅስቃሴ ስለሚጠይቅ፣ ግብዓቶችንም ማንቀሳቀስ የሚፈልግና በርካታ ተግባራቱ ንክኪ ያለባቸው በመሆኑ ለቫይረሱ መስፋፋት እንደሚያጋልጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶክተር) ተናግረዋል፡፡ ምርጫው የመንግሥትን ትኩረት በሽታውን ከመከላከል ወደ ምርጫ ተግባራት ሊያዞረውና የገንዘብ አቅምንም ሊቀንስ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ኤባ እንዳሉት በእርግጠኝነት የኮሮና ወረርሽኝ መቼ እንደሚገታ መናገር አይቻልም፡፡

እስካሁን በኢትዮጵያ ከውጭ ከሚገቡ ሰዎች ቫይረሱ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው በቅርቡ ግን በኅብረተሰቡ ውስጥ በሽታው እየተስፋፋ መሆኑ መረጋገጡንና ሁኔታውን ለማጥናት እየተሠራ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የቤተ ሙከራ (የላቦራቶሪ) አቅምን ማደራጀት፣ የጤና ሥርዓቱን ምንም ቀውስ ቢመጣ መቋቋም እንዲችል ማድረግ የሚጠይቁ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች በተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆናቸውን የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
Next articleኢትዮጵያ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡