በአማራ ክልል የዘረመል እና ሥነ ሕይዎት ጥናት እና መረጃ ማዕከል ተቋቋመ።

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጂኖሚክስ እና ባዮኢንፎርማቲክ (የዘረመል እና ሥነ ሕይዎት) መረጃ ማዕከል ተከፍቷል። ማዕከሉ የማንኛውንም በሽታ አምጪ ተህዋስ ምንነት በመለየት እና ከአጋር አካላት ጋር በመሥራት በክልሉ በጤናው ዘርፍ ጥናት እና ምርምር ለማድረግ እንደሚያስችልም ተነግሯል።

የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ተመርቆ የተከፈተው የዘረመል እና የሥነ ሕይወት ጥናት እና ምርምር ማዕከል መኾኑን ገልጸዋል። በፌደራል ጤና ሚኒስቴር የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግሎባል ፈንድ እና ሌሎች አካላት ድጋፍ የተቋቋመው ማዕከሉ ለዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ተቋማት የጥናት፣ ምርምር እና መረጃ ማዕከል አድርገው መጠቀም የሚችሉበት እንደኾነም ነው አቶ በላይ ያነሱት።

እንደ ኮቪድ 19 ያሉ አዳዲስ ወረርሽኝ ሲከሰቱ የበሽታውን አምጪ ተህዋስ ለመመርመር ያስችላል ነው ያሉት። በማዕከሉ ያሉ መሣሪዎች ወደ አዲስ አበባ ብሎም ወደ ውጪ ሀገር ለምርመራ ይላኩ የነበሩ የጤና፣ የሕክምና እና የምርምር ሥራዎችን በክልሉ ውስጥ መከወን እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

የኅብረተሰብን የጤና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ጥናት እና ምርምር ለማካሄድ ብሎም መድኃኒት የተላመዱ በሽታዎችን በማጥናት ከትባትን እስከ ማምረት ያደርሳልም ብለዋል። ማዕከሉ የተለያዩ በሽታዎች በሚከሰቱበት አማራ ክልል መከፈቱ ጠቀሜታው ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። አገልግሎቱ ለሀገርም ጭምር እንደኾነ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት በምርምር ማዕከሉ በመሥራት በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለማዕከሉ ውጤታማነት ሊተባበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። በማዕከሉ የተዘጋጀው መሣሪያ መረጃን መሠረት ያደረገ የመከላከል እና የማከም ሥራን ለመሥራት ያስችላል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ የተከፈተው የዘረመል ጥናት እና ምርምር ማዕከል ለሰው እና ለዕጽዋት የጤና ችግሮች ጥናት እና ምርምር በማድረግ ለሚወሰደው እርምጃ መረጃ የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል። የሚነሱ የጤና ወረርሽኞችን ምንነት በቴክኖሎጂው በመለየት ለመከላከል እና ለማከም መረጃ መስጠት እንዲሁም ጥናት እና ምርምር በማድረግ ችግሮችን አስቀድሞ በመለየት እና ለሚመለከተው በማድረስ መከላከል ማስቻል መኾኑንም አንስተዋል።

የጥናት ማዕከሉ እያደገ ሲሄድም ከወረርሽኝ በሽታዎች በተጨማሪ የኅብረተሰቡን የበሽታ ተጋላጭነቶች በዝርዝር በማጥናት ለጤናው ዘርፍ አስተዋጽኦው ጉልህ መኾኑን አንስተዋል። የፌደራሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሕዝቡን ከጤና አደጋ መታደግ አንዱ ሥራው መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ጌታቸው ከአማራ ክልል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተከፈተውን ማዕከል በ100 ሚሊዮን ብር የማሽን እና ሌሎች ቁሳቁሶች እና ግብዓቶችን እንዳሟላ ተናግረዋል። በዚህም ከማዕከሉ ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በቀጣይ በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ ማዕከሎችን እንደሚከፈቱ ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም በኮምፒዩተር የሚከናወኑ አነስተኛ ደረጃ ያላቸው 30 መሰል አገልግሎቶች እንደሚኖሩም አሳውቀዋል።

ማዕከሉን በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ፣ የአማራ ክልል የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እና በአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋና ጸሐፊ ታፈረ መላኩን (ዶ.ር) ጨምሮ የምርምር ተቋማት እና የአጋር አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አሥተዳደር ዐቢይ ጉባኤ አዲስ የዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎችን የሥነ-ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብን አጸደቀ።
Next articleየሜካናይዜሽን እርሻ በአማራ ክልል!