
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በላቀ የዳኝነት አገልግሎት በተምሳሌትነት የሚጠቀስ የዳኝነት ሥርዓት በክልሉ ውስጥ ዕውን ለማድረግ ሥር ነቀል የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም ገና ከጅምሩ አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ለመምራት የሚያስችሉ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው በክልሉ ምክር ቤት መጽደቃቸው ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ሕጎች መካከል የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017 አንዱ ነው፡፡
የአዋጁ መግቢያ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ዘላቂነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መኾኑን ይጠቅሳል፡፡ ይህም በክልሉ ውስጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራት እና ተገማችነት ያለው ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎትን በማስፈን የባለጉዳዮችን እርካታ ለማረጋገጥ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ አመኔታ የተቸራቸው ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት ያስችላል፡፡
የዳኞች ከለላ እና ጥበቃ በሕግ ዕውቅና ባለማግኘቱ ምክንያት ጥያቄው አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የክልሉ ዳኞች የዘመናት አንገብጋቢ ጥያቄ ኾኖ ቆይቷል፡፡ አዲሱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት መሪ ኀላፊነት ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ በተሠሩ በርካታ የምክክር እና የማሳመን ሥራዎች የዳኞች ከለላ እና ጥበቃ በክልሉ ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ በአዋጁ አንቀጽ 6 እና 7 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የዳኞች ከለላ እና ጥበቃ ዋነኛው ዓላማም ነጻ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያለው የዳኝነት አካልን ማረጋገጥ መኾኑ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡
ስለኾነም የዳኞች ከለላ እና ጥበቃ በሕግ ዕውቅና ማግኘቱ የዳኝነት ነጻነትን እና ገለልተኛነትን በማረጋጥ የላቀ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት እና በአንድ በኩል የባለጉዳዮችን እርካታ ያረጋገጡ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በማኅበረሰቡ ዕምነት ያተረፉ ፍርድ ቤቶችን በክልሉ ውስጥ ለመገንባት ያስችላል፡፡ የዳኝነት ነጻነትን እና ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ ከተወሰዱ መፍትሄዎች መካከል ቀደም ሲል በተለያየ ስያሜ ይጠሩ የነበሩ እና በአሥፈጻሚው አካል ሠብሣቢነት ይመሩ የነበሩ አደረጃጀቶች ቀሪ እንዲኾኑ እና በፍርድ ቤት ሠብሣቢነት የሚመራ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክን በበላይነት ማስተባበር እና መምራት አንዱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥልጣን እና ተግባር ኾኖ በአዋጁ አንቀጽ 5(7) ስር እንዲካተት ተደርጓል፡፡
የትብብር መድረኩን የሚመራ ጽሕፈት ቤት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ እንዲቋቋምም ተደርጓል፡፡ ይህም ቀደም ሲል የተለያዩ ሰበቦችን በመፈለግ የተለያዬ ስያሜ ባላቸው አደረጃጀቶች አማካኝነት በክርክር በተያዙ መዝገቦች ላይ ሳይቀር ግምገማ በማድረግ በዳኞች እና በዳኝነት አካሉ ላይ ይደረጉ የነበሩ ጣልቃ ገብነቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ነው፡፡
በተጨማሪም በክልል ደረጃ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎትን በመሠረታዊነት ለመለወጥ የተጀመረውን ሥራ የሚመራው የትራንስፎርሜሽን ዐቢይ ኮሚቴ በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች እንዲመራ መደረጉ በተመሳሳይ የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ ተብሎ የተወሰደ መልካም እርምጃ ነው፡፡
የዳኝነት ነጻነትን እና ገለልተኛነትን በማረጋገጥ ረገድ የውጭ ተጽዕኖ እና ጣልቃ ገብነትን መከላከል ብቻውን ግን በቂ አይኾንም ፡፡ ዳኞች ራሳቸው የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኝነትን ከሚጎዳ ተግባር መቆጠብ ብሎም የዚህ ዓይነት ተግባራትን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ሙያው የሚጠይቀውን የአንድ ጥሩ ዳኛ የሥነ ምግባር መመዘኛዎችን በማክበር ተግባራቸውን በትጋት እና በታታሪነት አንዳንዴ በማይመቹ ሁኔታዎች ውስጥ ኾነው ጭምር ለሙያው ታማኝ በመኾን ከሕዝብ የተሰጣቸውን ከፍተኛ ኀላፊነት እና አደራ እየተወጡ መኾኑ ይታወቃል፡፡ የዚያኑ ያህል ጥቂት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የዳኝነት ሙያ ከሚጠይቀው ሥነ-ምግባር ተቃራኒ በኾኑ ድርጊቶች ውስጥ ሲሳተፉ እና የዳኞችን፣ የዳኝነት ሙያን እና የፍርድ ቤቶችን ክብር ዝቅ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡
እንዲህ በኾነ ጊዜ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ሲኾን ፍርድ ቤቱም በተዘረጋው ሕጋዊ ሥርዓት መሠረት ራሱን በራሱ እያረመ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ነጻነት እና ተጠያቂነት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መኾናቸውንም ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የክልሉን ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የሥነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ በአዲስ መልክ ለማውጣት ምክንያት ኾኗል፡፡
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የሥነ-ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ ቁጥር 14/2007 በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ቢኾንም ግልጽነት የጎደላቸው ጉዳዮችን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፣ በአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን ውስጥ ረዳት ዳኞችን እና የሥነ ምግባር መርሆዎችን ያካተተ ቢኾንም በዝርዝር በማስቀመጥ ረገድ ውስንነት የታየበት በመኾኑ፤ የዲሰፒሊን ጥፋት ደረጃዎችን በማስቀመጥ ረገድ ግልጽነት የሚያንሳቸውን ድንጋጌዎች የያዘ በመኾኑ፣ በዲስፕሊን ክርክር ሂደት የዲሲፕሊን ክስ የቀረበበትን ዳኛ ወይም የጉባኤ ተሿሚ መሠረታዊ መብቶችን ለማክበር እና ለማስከበር የሚያስችሉ ዝርዝር የአሠራር ሥርዓቶችን መደንገግ በማስፈለጉ፣ የዳኞች ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና ቅሬታ ወይም አቤቱታ አቀራረብን የተመለከቱ ጉዳዮችን በደንቡ ውስጥ ማካተት በማስፈለጉ እና በሌሎች ምክንያቶች ደንቡ በአዲስ መልክ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አሥተዳደር ዐቢይ ጉባኤ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ሥብሠባ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘጋጅቶ በቀረበው የዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የሥነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ ላይ ተወያይቶ ደንቡን አጽድቆታል፡፡ ደንቡም ከፀደቀበት ግንቦት 05/2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባዊ እንዲኾንም ጉባኤው ወስኗል፡፡
በደንቡ ውስጥ በአዲስ መልክ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የዳኞች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓትን የሚመለከቱት ይገኙበታል፡፡ የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ምጥቀትን ተከትሎ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተበራከቱ እና የሰዎችን ቀልብ እየገዙ መጥተዋል፡፡ ዳኞች ከዚህ የቴክኖሎጂ ቱርፋት ተጠቃሚ መኾናቸው አይቀሬ ቢኾንም የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸው የዳኝነት ነጻነትን እና በተለይ ደግሞ ገለልተኛነትን የማይጋፋ መኾኑን የማረጋገጥ ኀላፊነት አለባቸው፡፡
የሌሎች ሀገራት ተሞክሮም ኾነ የዳበረው አስተሳሰብ እንደሚያሳየው የዳኞች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የዳኝነት ነጻነትን እና ገለልተኝነትን የማይጋፋ እና ማኅበረሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ሊያሳድር የሚገባውን አመኔታ የማይሸረሽር መኾኑን ማረጋገጥ የግድ የሚል መኾኑን ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ሞዴል የዳኞች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ደንቦች ተቀርጸው በበርካታ ሀገራት እየተተገበረ ይገኛል፡፡
የዳኝነት ሥነ ምግባር እና የዲጂታል ዘመንን በሚመለከት ጥናቶች እና ምርምሮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ሲደረጉ መታየቱ የዳኞች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ስለመኾኑ አመላካች ነው፡፡ በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚሠሩ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ከዚህ በፊት የነበረው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሲቃኝ ሁለት ገጽታ ያለው ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለበጎ ተግባር ሲጠቀሙበት የሚስተዋል ቢኾንም በተቃራኒው ጥቂት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሲቃኝ የዳኝነት ነጻነትን የሚጋፋ፣ ገለልተኝነትን ሳይኾን ወገንተኝነትን የሚያሳይ፣ ማኅበረሰቡ ለዳኞች እና ለፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን ዕምነት፣ ክብር እና ግምት ዝቅ እንዲል የሚያደርግ መኾኑን እንረዳለን፡፡ ስለሆነም የዚህ ዓይነት ግብረ ገብነት የጎደላቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞችን የሚከለክሉ ድንጋጌዎች በዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የሥነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል፡፡
በደንቡ ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያ ማለት በበይነ መረብ ላይ የሚገኙ መድረኮች ወይም መሳሪያዎች ኾነው በሰዎች መካከል መረጃ ልውውጥ፣ ዕይታዎች እና ይዘቶችን ለመጋራት፣ ለመፍጠር እና ለመተባበር የሚያስችሉ እንደ ፌስ ቡክ፣ ኤክስ፣ ቴሌግራም፣ ኢነስታግራም፣ ቲክ ቶክ፣ ሊንክድ ኢን፣ ስናፕ ቻት እና መሰል የማኅበራዊ ሚዲያዎችን የሚያጠቃልል ሲኾን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ማለት ደግሞ የይዘት አዘገጃጀት እና የጋራ ማድረግ፣ የተጠቃሚ ግንኙነት፣ በቀጥታ መግባባት፣ የማኅበራዊ አውታረ መረብ ግንባታ እና የመሳሰሉትን ያካትታል የሚል ትረጉም ተሰጦታል፡፡
በዚህም መሠረት ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ረገድ በደንቡ ውስጥ የሚከተሉት ፈቃዶች እና ክልከላዎች ተካተዋል፡-
✍️ ማንኛውም ዳኛ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሃሳቡን የመግለጽ መብት ያለው መኾኑን፤ ነገር ግን የፍርድ ቤትን ገለልተኝነት እና ነፃነት እንዲሁም ሕዝብ በፍርድ ቤት ወይም በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ዕምነት በሚሸረሽር መልኩ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ ዳኞች ገለልተኝነታቸው እና ነፃነታቸውን በሚነካ ወይም የሚነካ በሚመስል የሚዲያ አጠቃም ተግባር መገኘት የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ ዳኞች በፖለቲካ፣ በሃይማኖት ወይም አወዛጋቢ በኾኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በየትኛውም ማኅበራዊ ሚዲያ ሃሳብ መስጠት የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️. ዳኞች ማኅበራዊ ሚዲያ በሚጠቀሙበት ወቅት የሰዎችን ክብር በጠበቀ፣ ሙያን ባከበረ እና በቁጥብነት መኾን ያለበት ስለመኾኑ።
✍️ ዳኞች በመታየት ላይ ያለ ወይም ይፋ ያልተደረገ የፍርድ ቤት ጉዳይን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መለጠፍ፣ አስተያየት መስጠት ወይም መወያየት የማይችሉ ስመኾኑ።
✍️ ዳኞች በማኅበራዊ ሚዲያ የፖለቲካ ፓርቲ ተመራጭን፣ የፖለቲካ ፉክክሮችን ወይም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በመደገፍ ወይም በመቃወም መግለጽ የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ ዳኞች የአንድን ተቋም ምርት ወይም አገልግሎት የሚያስተዋውቁ ተግባራትን መፈፀም የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ዳኞች ሌሎችን ሊያስቆጡ የሚችሉ ፀብ አጫሪ ወይም ክብረ ነክ በኾነ መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ ዳኞች በፍርድ ቤት ተከራካሪ ከኾኑ ሰዎች፣ ዐቃቢያነ ሕግ፣ ጠበቆች፣ ተከላካይ ጠበቆች፣ ነገረ ፈጆች እና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ግንኙነት መፍጠር ወይም ሃሳብ መቀያየር የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ዳኞች ገለልተኝነታቸው ላይ ጥርጣሬ ሊፈጥር በሚችል መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን በጓደኝነት መወዳጀት፣ ገጻቸውን መከተል ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ በማኅበራዊ ሚዲያ መገናኘት የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ማንኛውንም ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በየትኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ ከማጋራት መቆጠብ ይኖርበታል፡፡
✍️ ዳኛ ግላዊ መረጃውን የራሱን ደኅንነት እና ገለልተኛነቱን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ከመግለጽ መቆጠብ ያለበት ስለመኾኑ።
✍️ ሃሰተኛ ማኅበራዊ ሚድያዎችን መጠቀም፣ መከተል፣ አባል መኾን ስለመከልከሉ።
✍️ ማንኛውም ዳኛ ማንነቱን ደብቆ ወይም ሃሰተኛ ማንነትን በመጠቀም የግል ወይም የቡድን ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም ወይም ማሥተዳደር የማይችል ስለመኾኑ።
✍️ የሚያስተዳድሯቸው አካላት የማይታወቁ ወይም በድብቅ የሚሠሩ የማኅበራዊ ሚድያዎች ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጋር ግንኙነት መፍጠርም ኾነ አባል መኾን የተከለከለ ስለመኾኑ፡፡
✍️የፍርድ ቤቱን ክብር እና ተዓማኒነት የሚጎዳ፤ የዳኞችን እና በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት መሪዎችን ስብዕና ክብር የሚያጎድፋ ማኅበራዊ ሚድያዎችን መጠቀም፣ መከተል እና አባል መኾን የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ ዳኞች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሥነ ምግባር ደንብን በጣሰ መልኩ በማኅበራዊ መዲያ የፃፉት፣ ያጋሩት ወይም በማንኛውም መንገድ የገለጹትን ሀሳብ እንዲያስተካክሉ በተጠየቁ ጊዜ ወዲያውኑ የማስተካከል ግዴታ ያለባቸው ስለመኾኑ ያካትታል፡፡
ሌላው በአዲሱ ደብን ውስጥ የተካተተው ዳኞች በውስጣዊ አሥተዳዳራዊ ጉዳዮች ማንኛውም ዓይነት ቅሬታ ወይም አቤቱታ ሲኖራቸው የሚያስተናገዱበትን ሥርዓት በተመለከተ ነው፡፡ የዳኞች አቤቱታ ወይም ቅሬታ አቀራረብ የዳኝነት ሙያን ክብር በሚመጥን አግባብ ሊኾን ይገባል፡፡ አቤቱታ ወይም ቅሬታ አቀራረቡ መደበኛውን ሥርዓት መከተል እና ምስጢራዊነቱን የጠበቀ መኾን አለበት፡፡
የሌሎች ሀገራት ልምድም ኾነ የዳበረው አሠራር የሚያመላክተው በዳኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች መደበኛውን የአቤቱታ ማቅረቢያ ሥርዓት የተከተለ መኾን የሚገባው መኾኑን ነው፡፡ በሰዎች ሕይዎት፣ ነጻነት እና ንብረት ላይ የመወሰን ሥልጣን እና ተግባር የተሰጠው ዳኛ ኢ-መደበኛ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓትን እና ማኅበረሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን አመኔታ በሚሸረሽር ሁኔታ ማቅረብ አይኖርበትም፡፡
ኢ-መደበኛ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት የዳኞችን እና የዳኝነት ሥርዓቱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ “አቤቱታ ወይም ቅሬታ” ማለት በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በፍርድ ቤት መሪዎች ወይም ባልደረቦቻቸው ላይ በዳኞች፣ በጉባኤ ተሿሚዎች፣ በረዳት ዳኞች እና በአሥተዳደር ሠራተኞች በኩል የሚቀርብ የትኛውም ጥያቄ እና አስተያየት የሚጨምር ስለመኾኑ በደንቡ ትርጉም ተሰጦታል፡፡
በየደረጃው በሚገኙ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ማንኛውም ቅሬታ ወይም አቤቱታ አለን ባሉ ጊዜ አቤቱታቸውን እያቀረቡበት ያለው መንገድ ሲታይ ሁለት መልኮች ያሉት መኾኑን እንረዳለን፡፡ በአንድ በኩል ብዙዎቹ ዳኞች መደበኛውን ሥርዓት የሚጠቀሙ ሲኾን፣ ጥቂቶች ደግሞ ኢ-መደበኛ የኾነውን የአቤቱታ አቀራረብ ሥርዓት ሲከተሉ ይታያል፡፡
በመኾኑም የዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር እና ማኅበረሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው ዕምነት ከፍ እንዲል ለማድረግ ያስችል ዘንድ የዳኞች አቤቱታ አቀራረብን በተመለከተ የሚከተሉት ጉዳዮች በደንቡ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል፡-
✍️ ዳኞች በፍርድ ቤት ተቋም ወይም በየደረጃው ባሉ የፍርድ ቤት መሪዎች ወይም በባልደረቦቻቸው ላይ የሚያቀርቡት ቅሬታ ወይም አቤቱታ ሲኖር ለዚሁ ተብሎ በተዘረጋ መደበኛ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት ምስጢራዊነትን፣ ቅሬታ የቀረበበትን አካል ክብር እና ሕዝብ በፍርድ ቤት ላይ ያለውን አመኔታ በጠበቀ መልኩ ብቻ መኾን ያለበት ስለመኾኑ፡፡
✍️ ዳኞች በፍርድ ቤቶች፣ በየደረጃው ባሉ የፍርድ ቤት መሪዎች ወይም የሥራ ባልደረቦቻቸው (ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች ወይም ሌሎች ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች ላይ) ያላቸውን ወይም ያቀረቡትን አቤቱታ ወይም ሌሎች ዳኞች ወይም የፍርድ ቤት ባልደረቦች ስላቀረቡት ወይም ስለሚያቀርቡት ቅሬታ ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በማንኛውም ሚዲያ በአደባባይ መግለጽ ወይም በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት የተከለከለ ስለመኾኑ፣
✍️ ዳኞች በተዘዋዋሪ መንገድ፣ በድብቅ ወይም መረጃ በማሾለክ የባልደረቦቻቸውን ወይም በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት መሪዎችን ክብር ለመንካት ወይም ዝቅ ለማደረግ የሚፈፀም ማንኛውም ተግባር የተከለከለ ስለመኾኑ።
✍️ ቅሬታዎችን ወይም የፍርድ ቤት ውስጣዊ ጉዳዮችን በውጫዊ የፖለቲካ ወይም የሚዲያ ጫና ለማስፈፀም የሚደረግ ተግባር የተከለከለ መኾኑን፤
የሚደነግጉ አንቅጽን የያዘ አዲስ የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የሥነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ በዳኞች አሥተዳደር ዐቢይ ጉባኤ የፀደቀ ሲኾን ደንቡ የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኝነትን የሚያስጠብቅ እንዲሁም ኅብረተሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን አመኔታ የሚያሳድግ ነው፡፡
ደንቡ ከፀደቀበት ግንቦት 5/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደንብ ቁጥር 1/2017 ኾኖ ተግባራዊ እንዲኾን በዐቢይ ጉባኤው የተወሰነ መኾኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በየደረጃው ያሉ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የፍርድ ቤት መሪዎች የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በዘርፉ ልምድ ካላቸው የሕግ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የሥልጠና መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲያደርግ ጉባኤው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን