ስለ ኩፍኝ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም ሕጻናት እንዲከተቡ በርብርብ እየተሠራ ነው።

30

ፍኖተ ሰላም: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኩፍኝ በከፍተኛ መጠን የሚተላለፍ እና ትኩሳት፣ ሽፍታ፣ ሳል፣ የዓይን መቅላት እና እንባን የሚያስከትል ከባድ በሽታ ነው። ያልተከተቡ ሰዎች፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ ከስድስት ወር በታች የኾኑ ጨቅላ ሕጻናት እና አነስተኛ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው ሰዎች ለኩፍኝ በሽታ በከፍተኛ ኹኔታ ተጋላጭ ናቸው።

በምዕራብ ጎጃም ዞን በሁሉም ወረዳዎች የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ተጀምሯል። ኩፍኝ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያለን ማንኛውም ሰው ሊያጠቃ የሚችል በሽታ መኾኑን በፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ባለሙያ ጌታነህ ክንዴ ገልጸዋል። በተለይም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናትን በከፍተኛ ኹኔታ የሚያጠቃ እና እስከ ሞት የሚያደርስ በሽታ ነው ብለዋል። በሽታው ሲከሰትም ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ መታከም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በፍኖተ ሰላም ከተማ 8 ሺህ 510 ሕጻናትን የኩፍኝ ክትባት ተጠቃሚ ለማድረገ እየሠራ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አያልነህ ስንታየሁ ተናግረዋል። ለዚህም ደግሞ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም ሕጻናት እንዲከተቡ በርብርብ እየተሠራ ነው ብለዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ለወረዳዎች ግብዓት ቀድሞ በማሰራጨት እና ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ እየተከናወነ መኾኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ክፍሌ ገልጸዋል።

ከኩፍኝ ክትባቱ ጎን ለጎን የነፍሰጡር እናቶች ክትትል እና የሥርዓተ ምግብ ልየታ ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። በዞኑ ከ220 ሺህ በላይ ሕጻናትን በኩፍኝ ክትባት ዘመቻው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል። ልጆቻቸውን ሲያስከትቡ ያገኘናቸው የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ከጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ በተፈጠረላቸው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ልጆቻቸውን በተደጋጋሚ በማስከተባቸው ከተለያዩ በሽታዎች እንዲጠበቁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ክትባቱን በተገቢው መንገድ የወሰዱ ሕጻናት በአካል እና በሥነ አዕምሮ ንቁ እንደሚኾኑ ገልጸዋል። የሕጻናት የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከግንቦት ከ6 እስከ 15/2017 ዓ.ም በንቅናቄ ይሰጣል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ
Next articleየጽንፈኝነት አስተሳሰቦች እና ተግባራትን በጋራ መታገል ይገባል።