ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሕጻናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከግንቦት 6 እሰከ 15/2017 ዓ.ም ድረስ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሚኾኑ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሕጻናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ ከኩፍኝ ክትባት በተጨማሪ የታመሙ፣ ክትባት ያላገኙ እና ያቋረጡ ሕጻናትን በመለየት ሕክምናና ክትባት ይሠጣል ብለዋል። መደበኛ ክትባትን የማስቀጠል ሥራም ይሠራል ነው ያሉት።

የሥርዓተ ምግብ እጥረት፣ የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል እና የቆልማማ እግር ችግር ያለባቸውን ሕጻናት በመለየት ሕክምና የሚሠጥ ይኾናል ብለዋል። የእናቶች ጤና አገልግሎት ላይም ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ነው ያሉት። ምክትል ኀላፊው እንደገለጹት አገልግሎቱን ለመሥጠት በክልሉ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፤ አስፈላጊ ግብዓትም ቀርቧል ብለዋል።

ለዘመቻው ውጤታማነት ደግሞ ማኅበረሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም አማካሪ ማስተዋል ቀረብህ ሕጻናትን ከሞት እና ከአካል ጉዳተኝነት ለመከላከል ከመደበኛ ክትባት ባለፈ የማጠናከሪያ ክትባት በዘመቻ እየተሠጠ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ዘመቻም በሀገር አቀፍ ደረጃ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾኑ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሕጻናት እንደሚከተቡም ገልጸዋል። ከኩፍኝ ክትባት ባለፈ የእናቶችን እና ሕጻናትን ህመም፣ ሞትን እና አካል ጉዳትን ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንደሚሠራም ነው የገለጹት። የሃይማኖት አባቶች እና ማኅበረሰቡ ክትባቱ በውጤት እንዲጠናቀቅ እንዲያግዙ አሳስበዋል።

በማስጀመሪያው ላይ ያገኘናቸው እናቶች ከዚህ በፊት ልጆቻቸውን ማስከተባቸውን ነግረውናል። ሌሎች እናቶችም በሽታውን ከባሕል ጋር ከማያያዝ ወጥተው ልጆቻቸውን በማስከተብ ሊያጋጥም የሚችለውን የአካል ጉዳት እና ሞት መከላከል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየቀደመ ባሕልን በመጠቀም ችግሮችን መፍታት ይገባል።
Next article“ሁሉን የሚያግባባ ነገር ፈልጉና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ፍቱ፣ በዚህ አማራጭ እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ አድርጉ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ