በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

29

እንጅባራ:ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በእንጅባራ ከተማ ከሚገኙ የመንግሥት እና የግል ኮሌጆች ምሁራን ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል። በመድረኩ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የደረሰው ጉዳት እና ከችግሩ መውጫ መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ሰውነት በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ ኅብረተሰቡ ለዘመናት ለፍቶ የገነባቸውን ተቋማት ያወደመ፤ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች ዘንድ የቆዩ መልካም እሴቶች እንዲሸረሸሩ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

በየደረጃው በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ኅብረተሰቡ ግጭቱ ያደረሰውን ጉዳት በውል የተረዳበት እና ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳየበት ነው ብለዋል። የኅብረተሰቡን አጋርነት ከጸጥታ መዋቅሩ ቁርጠኝነት ጋር በማቀናጀት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው ግጭቱ ካደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ባሻገር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል የክልሉን እድገት እየገታ ነው ብለዋል። ግጭቱ በጊዜ ካልተገታ የሚያደርሰው ሁለንተናዊ ቀውስ የከፋ እንደሚኾን ያነሱት አቶ ግዛቸው ምሁራን ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከት እና ለሰላም ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በክልሉ እየተደረገ ያለው አውዳሚ የትግል አካሄድ ክልሉን ከችግር የሚያወጣ ሳይኾን የክልሉን ሕዝብ ለተወሳሰበ ችግር የሚዳርግ መኾኑን ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ከተራዘመ ስቃይ እንዲገላገል ሰላማዊ ድርድሮችን ማስቀደም እንደሚገባም አንስተዋል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመስቀለኛ ጥያቄ ለምን እና እንዴት?
Next articleየቀደመ ባሕልን በመጠቀም ችግሮችን መፍታት ይገባል።