መስቀለኛ ጥያቄ ለምን እና እንዴት?

89

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዕለት ከዕለት ሕይዎታችን ውስጥ እንኳን “መስቀለኛ ጥያቄ” የሚለው ሐረግ አስፈሪ እና አስደንጋጭ ነው፡፡ መስቀለኛ ጥያቄ ሲባል ጠያቂዎች ተጠያቂዎችን ጠምዝዘው ወጥመድ ውስጥ እንደሚያስገቡ ተደርጎ ስለሚወሰድ ብዙ ጊዜ ብዥታ ውስጥ የሚያስገባ ትርጓሜ ያለው ይመስላል፡፡

መስቀለኛ ጥያቄ ሲነሳ ዊግሞር የተባለው አሜሪካዊ የሕግ ምሁር የጠቀሰው ነገር አብሮ ይነሳል፡፡ “መስቀለኛ ጥያቄ እውነትን ፈልፍሎ ለማውጣት የተፈጠረ ትልቅ የሕግ ሞተር ነው” ይለዋል፡፡ በእርግጥ ዊግሞር መስቀለኛ ጥያቄን አሽሞነሞነው እንጅ በሚገባ አልበየነውም ብለው የሚሞግቱ የዘርፉ ምሁራንም አሉ፡፡

በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ውስጥ “ጥያቄ” የመረጃ እና ማስረጃ መፈልፈያ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ “ምስክሮች የፍትሕ ሥርዓቱ ዐይን እና ጆሮ ናቸው” ያሉን የክልል ዐቃቤ ሕግ የኾኑት አቶ ወንዳቸው ሠራው በፍርድ አደባባይ ከሳሽ ወይንም ተከሳሽ፤ ዐቃቤ ሕግ ወይም ጠበቃ የያዙትን ጭብጥ ያስረዱልናል የሚሏቸውን ጥያቄዎች ለምስክሮች ያቀርባሉ፡፡

በወንጀልም ኾነ በፍትሐብሔር የክርክር ሥነ ሥርዓት ውስጥ የሚቀርቡ አራት ዓይነት ጥያቄዎች አሉ ያሉት አቶ ወንዳቸው ዋና ጥያቄ፣ መስቀለኛ ጥያቄ፣ ድጋሜ ጥያቄ እና ማጣሪያ ጥያቄ ይባላሉ ነው ያሉት፡፡ አራቱም ጥያቄዎች የየራሳቸው የኾነ ዓላማ እና ግብ አላቸው ያሉን ደግሞ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው ጉባይ አሰፋ ናቸው፡፡

የሕግ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በእኛ ሀገር የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ በርካቶቹ የክርክር ጉዳዮች መቋጫ የሚያገኙት በሰው ምስክርነት ላይ ተመሥርተው በመኾኑ መስቀለኛ ጥያቄ ለፍትሕ ሥርዓቱ ወሳኝ ነው፡፡ በመኾኑም መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብ የጉዳዩን ጭብጥ በትክክል እና በጥንቃቄ ለመለየት ያገለግላሉ፡፡
መስቀለኛ ጥያቄ ከሳሽ ምስክር አቅርቦ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ በተከሳሽ፤ በመከላከያ ምስክር ማሰማት ወቅት ደግሞ ተከሳሽ ዋና ጥያቄ አቅርቦ ከሳሽ መስቀለኛ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ መስቀለኛ ጥያቄ አቅራቢው የምስክሩን እና የምስክርነት ቃሉን ተገቢነት ለማረጋገጥ በንቃት፣ የጥያቄውን እና የመልስ ተዛምዶ እና ተገቢነትን በአግባቡ ማጤን ይጠይቃል ነው ይላሉ፡፡ በወንጀልም ኾነ በፍትሐብሔር የክርክር ሂደቶች መስቀለኛ ጥያቄ ይቀርባል ያሉት የክልል ዐቃቤ ሕጉ የመስቀለኛ ጥያቄ ወሰኑ በዋና ጥያቄ ላይ የተመሠረተ ይኾናል ይላሉ፡፡

መስቀለኛ ጥያቄን ከዋና ጥያቄ ልዩ የሚያደርገውም በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት መሪ ጥያቄ ማቅረብ መቻሉ ነው፡፡ መሪ ጥያቄ ማለትም ጠያቂው ምስክሩን ወደሚፈልገው ጭብጥ እንዲሄድለት መምራት እንደኾነ ባለሙያው ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ጉባይ አሰፋ እንደሚሉት የመስቀለኛ ጥያቄ ዋና ጥያቄን ተከትሎ የሚመጣ መኾኑን ተከትሎ መስቀለኛ ጥያቄ አለመጠየቅ ይቻላል፡፡

መስቀለኛ ጥያቄ ከክርክሩ አውድ ከወጣ፣ ከሞራል እና ከሕግ አግባብ ተገቢነት ከሌለው የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ቀርቦ ሊቋረጥ ይችላል ብለውናል፡፡ በጥቅሉ ይላሉ የሕግ ባለሙያዎቹ የፍትሕ ሥርዓቱን ተገቢ እና ትክክለኛ ለማድረግ የምስክር አስፈላጊነት ወሳኝ ነው፡፡ መስቀለኛ ጥያቄ ደግሞ የሕግ እሳቤ መኾኑን እና የፍትሕ ሥርዓቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚቀርብ ቴክኒካል እና በሳል አቀራረብ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleተቋማትን በማዘመን የተናበበ የሥራ ምኅዳር ለመፍጠር እየተሠራ ነው።
Next articleበክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።