
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በከተማ ዘርፍ የሚገኙት የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን እና የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ባለፉት ጊዜያት የሠሯቸውን ሥራዎች አስመልክተው በጋራ መግለጫ ሠጥተዋል። የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ወርቁ ያየህ ከሌሎች 16 ከሚኾኑ ተቋማት ጋር በከተማ ዘርፍ በመታቀፍ አብሮ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ ተቋማትን የማዘመን ሥራ ነው ብለዋል። በዚህም ከፍተኛ የኾነ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል በአስራ አራት ዞኖች የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ አገልግሎት አሰጣጥ በሲስተም የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በክልሉ አስራ አራት የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መኖራቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ማዕከላት ከዚህ በፊት ዲጂታላይዝድ አልነበሩም ነው ያሉት።
አሁን ላይ ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ ከባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል ነው ያሉት። ይህም የትራፊክ አደጋን 80 በመቶ ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። ሁለተኛው የኢ-ቲኬቲንግ ሲስተም አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ይህ ሲስተም በአማራ ክልል ውስጥ ባሉ አስራ አራት በሚኾኑ መነኻሪያዎች ተግባራዊ ኾኗል ነው ያሉት። በዚህም አላስፈላጊ የታሪፍ መጨናነቅ ማስቀረት፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣ ተሽከርካሪዎች በወንበር ልክ እንዲጭኑ ማድረግ እና ከመናኸሪያ ወከባ እና ግርግር በመቀነስ ለተጠቃሚዎች ምቹ እንዲኾን አግዟል ብለዋል።
ሦስተኛው ዘመናዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማሳደግ ነው። በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማት ግንባታ እየተገነባ ነው፣ ይህ ልማት ዘመናዊ ከተማን ታሳቢ ያደረገ ግንባታ ነው ብለዋል። በዚህም በዘመናዊ ከተማ የዘመነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ወርቁ ሞተር አልባ የኾኑ ትራንስፖርቶችን መሠረት ያደረጉ መንገዶች እንዲገነቡ ምክረ ሀሳብ፣ ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ አቤል ፈለቀ በክልሉ ካሉ የተለያዩ ተቋማት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በክልል ደረጃ የቴክኖሎጂ ልማት እና የመሠረታዊ ፍላጎትን በሚያሳካ እና በሚመልስ መልኩ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም በተለያዩ ተቋማት በኦንላይን የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማልማት የመንግሥትን ወጭ የሚቀንሱ፣ የተገልጋይን ርካታ የሚያረጋግጡ፣ የተገልጋይን ድካም የሚቀንሱ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ፣ የተሳለጠና የተናበበ የሥራ ምኅዳርን የሚፈጥሩ ሲስተሞች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህም እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ድረስ በአብዛኞቹ ወደ ሥራ በማስገባት ተግባራዊ ይኾናሉ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሠናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን