
ጎንደር: ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ ያጋጠመውን የሰላም እጦት ችግር በመቀልበስ የማኅበረሰቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለመ ውይይት ተካሄዷል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት ዞኑ ከነበረበት ውስብስብ ችግር ወጥቶ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ማግኘት ተችሏል።
በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የጸጥታ ችግር ያለ በመኾኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባልም ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው። የጥፋት ኀይሉ በፈጸመው ተግባር የመንግሥት ሠራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ እየታፈኑ፣ እየተደበደቡ መስዋዕትነት ከፍለዋልም ብለዋል።
የጥፋት ኀይሉ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን እያወደመ የአማራ ሕዝብ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዳይደርስ እና በዞኑ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ አድርጓል ነው ያሉት። የጤና ባለሙያዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሕጻናትን እንዳይከትቡ አድርጓል ያሉት አቶ አወቀ በክትባት እጦት ሕጻናት ለበሽታ እና ሞት እንዲዳረጉ ኾነዋል ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የጋራ አላማን በመፍጠር የአማራን ሕዝብ ተጠቃሚነት እና ሰላም ሊያረጋግጡ ይገባልም ብለዋል። የፓለቲካ ልዩነት ቢኖር እንኳን ሀገርን አንድ የሚያደርግ፣ የአማራን ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የሰላምን አማራጭ ማስቀደም እና ማጽናት ይገባል ነው ያሉት።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ልህቀት ዲዛንይን እና ቁጥጥር ሥራ ኮርፖሬሽን አማካሪ ፍቃዴ ዳምጤ (ዶ.ር) አንጻራዊ ሰላም መኖርሩ የመንግሥት ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ አገልግሎትን ለማግኘት መብቱን ማስጠበቅ እና ከእጅ መንሻ መራቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በዞኑ ያጋጠመውን የሰላም እጦት ችግር በመቀልበስ የማኅበረሰቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለመ ውይይት መደረጉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ ገልጸዋል። መንግሥት ሠራተኞች በተሠማሩበት ሙያ ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ሰላም እንዲጸና የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አብራርተዋል። ሰላምን ለማጽናት ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አቡየ ካሳው የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ እና ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ሰላምን ለማጽናት የበኩሉን እየተወጣ መኾኑን ተናግሯል።
ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ወይንሸት አያሌው የመንግሥት ሠራተኞች ሙያዊ መርኾችን በማክበር እና በእኩልነት በማገልገል ሰላም እንዲጸና እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።
የአማራን ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የሰላምን አማራጭ ማስቀደም እና ማጽናት እንደሚገባ በውይይቱ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን