መምህራን ትምህርት የሚያስተጓጉሉ ኀይሎችን ማውገዝ እንደሚገባቸው ተመላከተ።

35

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከሚገኙ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ የትምህርት መሪዎች እና የአሥተዳደር ሠራተኞች ጋር “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት ተካሂዷል። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ በክልሉ በጽንፈኛ ኀይሉ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ በክልሉ የደረሰውን ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ የጉዳት መጠን በተገቢው ሁኔታ ለማስገንዘብ መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ወደ ትምህርት ቤት ያልተመለሱ በርካታ ተማሪዎች አሉ ያሉት አቶ ሲሳይ ይህ ደግሞ በክልሉ ላይ ከፍተኛ ችግር አድርሷል ነው ያሉት፡፡

ትምህርት እና ፖለቲካ በምንም መመዘኛ አንድ አለመኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ክልሉን ለዘርፈ ብዙ ጉዳት መዳረጉንም ተናግረዋል፡፡ ጠመኔ የያዙ እና ነጭ ጋዎን የለበሱ የዕውቀት አባቶች እና እናቶች በታጣቂው ኀይል ክብረ ነክ በኾነ ሁኔታ ተንበርክከዋል፤ ታግተዋል፤ መስዋዕትም ኾነዋል ነው ያሉት፡፡

የጥፋት ቡድኑ የፈጸመውን ይህን እኩይ ድርጊት እና አስነዋሪ ምግባርም መምህራን አጥብቀው ማውገዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ”ሰላም ዝም ብሎ ሊመጣ አይችልም” ያሉት አቶ ሲሳይ ለሰላም ቀናኢ የኾነ ዜጋ ሁሉ መነጋገር፣ መደማመጥ እና የመፍትሔው አካል መኾን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የመማር ማስተማሩ ሥራ የተሳለጠ እንዲኾንም መምህራን ከማስተማር ባሻገር ሰለም እንዲሰፍን የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ውይይቱ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አሳታፊ በኾነ መልኩ እንደቀጠለም አንስተዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት ትምህርትን በከፍተኛ ኹኔታ እንደፈተነው ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች በተሟላ መንገድ እንዳያስተምሩ፣ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ ማድረጉንም አመላክተዋል። መምህራን እንደሚታፈኑ እና እየተደወለ ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው ገልጸዋል። የሕጻናትን የመማር መብት እስከ መገደብ የደረሰው ታጣቂ ቡድን በእጅጉ መወገዝ ይኖርበታል፤ ሰላም እንዲመጣም መላው ማኅበረሰብ አጥብቆ እንዲሠራ መምሪያ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ የመምህራን ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚ መኮንን ደርሶ ሰላምን የማይፈልግ ማንም ሰው የለም ብለዋል፡፡ መምህራን የሰውን ልጅ ከመቅረጽ ውጭ ሌላ ተግባር የላቸውም ነው ያሉት፡፡ የመንግሥት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በተዘጉበት አካባቢዎች ሳይቀር መምህራን ችግሮችን እየተጋፈጡ በማስተማር ላይ መኾናቸውን ሥራ አሥፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ሰላም እንዲሰፍን የመምህራን ድርሻ የሚኾነው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ተግባር ውጭ በሚያገኙት አጋጠሚ ለተማሪዎች ስለ ሰላም ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሕዝቡ አንድነት እና ከመሪው ጋር ያለው መናበብ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻሉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።
Next articleየመንግሥት ሠራተኞች በጋራ በመቆም ሰላምን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር አሳሰበ።