
ሁመራ፡ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ከተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሁመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን አማካሪ ጥላሁን ዓለምነህ የዞኑ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሠለፍ ክልሉ የገጠመውን ችግር በውይይት እና በንግግር እንዲፈታ እያደረገው ያለው ተሳትፎ ሊበረታታ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ለውጡ ለዞኑ ሕዝብ ያመጣውን የነፃነት እድል የሚፈታተኑ ውጫዊ እና ውስጣዊ ችግሮች መከሰታቸውን ያነሱት አቶ ጥላሁን ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በትብብር መቆም አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ተከዜ የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ድንበር መኾኑን ገልጸዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከዚህ በፊት የነበረውን ትጋት እና ቁርጠኝነት በማስቀጠል የማንነቱን መነሻ እና መዳረሻ በውል የተረዳ መኾን እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል። ሕዝቡ ትናንት ያለፈበትን የትግል እና የበደል ዘመናት በማሰብ የሀገር አንድነትን ለማጠናከር የሚደረገውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ነፃነቱን ካረጋገጠ በኋላ አማራነቱን አስጠብቆ፣ ማንነቱን አረጋግጦ ለሰላም እና ለልማት መቆሙን አንስተዋል። ሕዝቡ ነፃነቱ ያመጣውን ዕድል በአግባቡ እንዳይጠቀም የሚያደርግ የውስጥ እና የውጭ ያልተገባ ግጭት ፈላጊ ኀይሎች የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማወክ ሙከራ እያደረጉ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ይኹን እንጂ ማንኛውም አካል ቢኾን ማንነቱን አሳልፎ የሚሰጥ እንቅስቃሴን ሕዝቡ አምርሮ በመታገሉ ዞኑ ፍጹም ሰላም እንዲኾን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል። የሕዝቡ አንድነት እና ከመሪው ጋር ያለው መናበብ ተጠናክሮ መቀጠሉ የዞኑን ሰላም እና ልማት ዘላቂ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት።
ማንነት የሥነልቦና እና ተፈጥሮአዊ ጉዳይ በመኾኑ ያለፈቃድ ሊጫንበት አይገባም ያሉት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር ዋና ሥራ አሥኪያጅ ገሠሠው ወንድም (ዶ.ር) ናቸው። አዲስ የምንጠይቀው ማንነት የለንም ያሉት ሥራ አስኪያጁ ነባር አማራዊ ማንነታችን ሕጋዊው እውቅና እንዲሰጠው ነው ጥያቄአችን ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌ አቶ ሰረበ በየነ አባቶቻችን ለዚህ ሕዝብ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። እነሱ በብዙ ዋጋ ጠብቀው አስረክበውናል፣ እነሱ የከፈሉትን ዋጋ ክብር በመስጠት ለመጭው ትውልድ ከነክብሩ ማስረከብ አለብን ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ ማንነት፣ ባሕል እና ትውፊት ለልጆቻቸን ማስተማር አለብን። ለሰላም እና ለልማት በጋራ መቆም ጊዜው የሚጠይቀው ትልቅ ጉዳይም ነው ብለዋል።
ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም እኛ አማራዎች ነን። ማንነታችንን ዳግም አሳልፈን አንሰጥም። የውስጥ ሰላማችንን በማዎክ ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለሚሰጠን ኀይል ዕድል አንሰጥም ብለዋል። መሪዎች እና ሕዝቡ ተጨባጭ ተግባራትን በማከናወን ሰላምን ማጽናት እና ማንነትን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን