የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።

14

ጎንደር: ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ባለፉት ጊዜያት በተቋማት የአካቶ ተግባራት መመዘኛ ባለመኖሩ አገልግሎቱን ውጤታማ ለማድረግ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር አንስተዋል። አሁን ላይ የተቋማትን የአካቶ ትግበራ በሕግ ማዕቀፍ በማስገባት እና የተጠያቂነት ሥርዓትን በመዘርጋት የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የተቋማትን አካቶ ትግበራ አሠራር እና ሂደት ውጤታማ ለማድረግ ቢሮው በጎንደር ከተማ ለዞን እና ለወረዳ መሪዎች ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በቀጣይም በክልሉ በ40 ተቋማት የአካቶ ትግበራ ምዘና እንደሚደረግም ተናግረዋል። ሥልጠናው የሠልጣኞችን ዕውቀት የሚያሳድግ መኾኑን የገለጹት ኀላፊዋ በቀጣይ በትኩረት እንዲሠሩ መነሳሳትን እንደሚፈጥር አስገንዝዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊ አቶ ያምራል ዋሴ የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት ተግባራዊ መደረጉ ለሥራው ውጤታማነት አጋዥ መኾኑን አንስተዋል። ሌላኛዋ የሥልጠናው ተሳታፊ ሃረግ ደሳለኝ ተቋሙ ብቻውን የሚሠራው ሥራ በቂ ባለመኾኑ ሌሎች ተቋማት እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የሚፈለግበት ደረጃ ላይ መድረስ የሚቻለውም በቅንጅት በመሥራት በመኾኑ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንደኾኑ ተናግረዋል። በሥልጠናው ዕውቀት እና ልምድም ማግኘታቸውን አንስተዋል። ከሥልጠናው ያገኙትን ልምድ በመጠቀም የሴቶች የሕጻናት የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

ተቋማት ለአካቶ ትግበራ ሥራ ትኩረት በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉም ጥሪ ቀርቧል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመምህራን በትምህርት ቤቶች ሰላምን መስበክ ይገባቸዋል።
Next articleየሕዝቡ አንድነት እና ከመሪው ጋር ያለው መናበብ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻሉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።