መምህራን በትምህርት ቤቶች ሰላምን መስበክ ይገባቸዋል።

21

ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ የትምህርት መሪዎች እና የአሥተዳደር ሠራተኞች “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከፖለቲካ ንክኪ ነጻ የኾኑ ዕውቀት መጋቢ መምህራን እና ተማሪዎች በጥፋት ኀይሎች ታፍነው ተወስደዋል፤ ቆስለዋል፤ ተገድለዋልም ብለዋል።

የጥፋት ኀይሎች በእኩይ ምግባራቸው የአማራን ሕዝብ ወደ ቁልቁለት ጉዞ መርተውታል ያሉት አቶ ጎሹ አሁን ደግሞ ከአማራ ሕዝብ የውስጥም የውጭም ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ለተጨማሪ ጥፋት እየተሯሯጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለውም መምህራን እና የአሥተዳደር ሠራተኞች ለሰላም ዘብ በመቆም ስለሰላም የመስበክ እና ሀገርን የማስቀጠል ታሪካዊ ብሎም ሙያዊ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት። የጥፋት ኀይሎች ከባዕዳን የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር አማራን ለማጎሳቆል ብሎም ለማጥፋት የሚያደርጉትን ደባ መምህራን አጥብቀው በማውገዝ መቃወም አለባቸው ብለዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ በአንድ እጁ ሰላምን እያሰፈነ እና እያጸና በሌላ እጁ ልማትን በማሳለጥ ባሕር ዳር ከተማ ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ ለጎብኝዎች የምትመረጥ ብሎም በአፍሪካ ተመርጣ የምትጎበኝ ውብ ከተማ ለማድረግ እየተጋ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። እንደማሳያ በኮሪደር ልማት አበረታች ውጤት ተመዝግቧልም ነው ያሉት።

የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የጥፋት ኀይሎች በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ቦንብ በማፈንዳት መማር ማስተማሩ እንዲስተጓጎል እድርገው እንደነበርም አስታውሰዋል። ይሁን እና ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነጻ በመኾኑ የጥፋት ኀይሎችን እኩይ ምግባር መምህራን ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።

በውይይቱ ከፍተኛ የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሕዝቡ ሰላሙን በማስከበር ልማቱን ለሚያስቀጥሉ መሪዎቹ ድጋፉን እንደሚሰጥ የዱርቤቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleየሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።