ሕዝቡ ሰላሙን በማስከበር ልማቱን ለሚያስቀጥሉ መሪዎቹ ድጋፉን እንደሚሰጥ የዱርቤቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

25

ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር ለሁለተኛ ዙር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ተመርቀዋል። የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ የሰሜን ጎጃም እና የደቡብ አቸፈር ወረዳ መሪዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የኮሪደር ልማት እና የሁለገብ ስታድየም ግንባታ ሥራዎች ተመርቀዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በሪሁን ቢረሳው ስለ ልማት ሥራዎቹ በሰጡት መረጃ በከተማዋ የማኅበረሰብ ተሳትፎን ጨምሮ ከ322 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። ቃል ከተገቡት 18 ሥራዎች ውስጥ በ185 ሚሊዮን ብር የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ በ3 ሚሊዮን ብር የተገነባ እና በሂደት ላይ ያለ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ስታድየም፣ በ15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የተገነባ 742 ሜትር የጌጠኛ መንገድ፣ በ17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነባ የኮሪደር ልማት፣ በ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን የማሳደግ ሥራ፣ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ድልድይ፣ የቁጠባ ቤቶች፣ የአውቶቡስ መናኻሪያ መጸዳጃ ቤት፣ የመንገድ ዳር መብራቶች እና ኮንቴይነሮችን ለተገቢ ወጣቶች የማስተላለፍ ሥራ መሠራታቸውን ዘርዝረዋል።

የሆስፒታሉ ትላልቅ የሕክምና ቁሳቁሶች መሟላታቸውን የገለጹት ከንቲባው በቀጣይም ከተማዋን ስማርት ሲቲ የማድረግ ሥራ መጀመሩን፣ የመናኻሪያ ኢ – ቲኬቲንግ አገልግሎት ፕሮጀክት እንደሚጀመር ተናግረዋል። የዱርቤቴን ሕዝብ የበለጠ ለማገልገል የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ የመስጠት፣ የትምህርት ቤት፣ የድልድይ ግንባታ እና የቄራ አገልግሎት ግንባታ፣ የከተማ አሥተዳደር ቢሮ ግንባታ፣ ሲሲቲቪ ካሜራዎች የመግጠም እና የአውቶቡስ መናኻሪያን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ከንቲባው የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር ወደ መካከለኛ ከተማ አሥተዳደር እንድታድግ፣ የዓለም ባንክ ልማት ተጠቃሚ እንድትኾን፣ የኔትወርክ ማስፋፊያ እንዲሠራ፣ ተጨማሪ የውኃ ጉድጓድ እንዲኖር፣ የሆስፒታሉ ደረጃ ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲያድግ፣ ከዱርቤቴ – ቁንዝላ የአስፋልት መንገድ ሥራ እንዲፋጠን እና የደረቅ ወደብ እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

ሰላም እና ልማትን በዱርቤቴ ለማረጋገጥ እየሠራን ነው፤ ነገር ግን በሥራ ሂደት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ ችግሮቹን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ሠርተን እናልፋለን ነው ያሉት። በአንድነት ቆመንም ችግሮችን እንፈታለን ብለዋል። መፍትሄ ማምጣት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይኾን ሁላችንም ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሄ ማምጣት አለብን ብለዋል።

አሁን ላይ በአስተሳሰብ ልህቀት እንጂ ጫካ በመግባት ለውጥ እና ልማት ስለማናመጣ ጫካ የገቡ ወንድሞቻችን ወደ ሰላም እና ውይይት መምጣት አለባቸው ብለዋል። የጸጥታ ጥምር ኃይል እና መከላከያ ሠራዊት ሰላማችን ስላጸኑልን እና በመስዋዕትነት ሀገራችን እና ሰላማችን ስለሚጠብቁ እናመሠግናለን ነው ያሉት።

አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች አቶ ታደለ አላምረው እና አቶ ጥላሁን የኔነህ በተሠሩት መሠረተ ልማቶች መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሕዝቡ በራሱ አቅም በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን መገንባቱን አስታውሰው መንግሥትም ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን በመሥራቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ተናግረዋል።

በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ ልማት መሠራቱም የሚደነቅ ነው፤ ተጠናክሮ ይቀጥልም ብለዋል። የሚታይ ልማት በመሠራቱ ወጣቱ መደሰቱን ገልጸው ሕዝቡ ሰላሙን በማስከበር ልማቱን ለሚያስቀጥሉ መሪዎቹ ድጋፉን እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ተቋማዊ ነጻነት እንደተጠበቀ ኾኖ በጋራ እና በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው ተጠቆመ።
Next articleመምህራን በትምህርት ቤቶች ሰላምን መስበክ ይገባቸዋል።