
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የዳኝነት እና ፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በጋራ የመሠረቱት የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ተቋማቱ ተቋማዊ ነጻነታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ በጋራ እና በትብብር ለመሥራት ነው ተብሏል።
ከአንድ ተቋም ላይ የሚፈጠር ችግር የፍትሕ ሥርዓቱን ያዛባል ያሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በመግባባት፣ በትብብር እና በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል።
የትብብር መድረኩ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ማስተባበሪያ ቻርተር ተፈራርሞ ወደ ሥራ መገባቱም ተነስቷል። በቻርተሩ 38 አጀንዳዎች ተለይተው እና 16 ዓይነት እቅዶች ተዘጋጅቶለት ወደ ሥራ በገባባቸው ያለፉት ዘጠኝ ወራት ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል ተብሏል።
የትብብር መድረኩ ከፌደራል እና ከሌሎች ክልሎች ልምድ እና ተሞክሮ በመቅሰም አበረታች ሥራዎች እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ታይተዋል ያሉት አቶ ዓለምአንተ ለውጡን በየጊዜው እየገመገሙ እና ክፍተቶች ሲኖሩም እያረሙ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የትብብር መድረኩ ዓላማ የፍትሕ አሥተዳደር ውጤታማነትን ማሳደግ፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብት መከበርን ለማረጋገጥ በትብብር መሥራት እንደኾነ በሪፖርቱ ተነስቷል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!